1
Home    News     States     Investment     Tourism     Sport    Entertainm.    Radio & Tv     About us     Contact      Links     Archives
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
admin@hebrezema.info
ኢትዮጵያ ወደቀድሞ ገናናነቷ ለመመለስ የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ እያፋጠነች ነው ዜና ትንታኔ
ከብሩህ ኮከብ በህር ዳር/ኢዜአ/
18 July 2013
የአኩስም ሐውልቶችን ፈልፍለው ያቆሙ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ
ክርስቲያናትንና የጎንደር አብያተ መንግስታትን ያነፁ ትውልዶችን
ያፈራችና በስልጣኔ ማማ ላይ ከነበሩ ሀገሮች ተርታ ተሰልፋ ገናናነቷን
ያስመሰከረች ሀገር ነበረች ኢትዮጵያ፡፡

በአንድ ወቅት በዓለም ላይ ቀደምት የስልጣኔ ቁንጮ ላይ ከነበሩ ሀገሮች
ተርታ ተሰልፋ የነበረችው ታላቅና ገናና ሀገር እንዳለመታደል ሆኖ
በተለያየ ወቅት በተፈጠረ የውስጥና የውጭ ችግር ላለፉት ዘመናት የችግር
ተምሳሌት ተደርጋ ስትጠቀስ ኖራለች፡፡

የቀድሞ ገናናነቷን ለመመለስ አገሪቱን አሁን እያስተዳደረ የሚገኘው
መንግስት መሪ የነበሩት በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ
አማካኝነት በሁሉም የልማት መስኮች የጠራ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፋ
ወደተግባር ከተሸጋገረች አመታትን አስቆጥራለች፡፡ ለዘመናት በድህነት
ስትማቅቅ ከነበረችበት አዙሪት ኢትዮጵያ ተላቃ ላለፉት 10 ተከታታይ
ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ የቀድሞ ገናናነቷን
ለመመለስ እየታተረች ትገኛለች፡፡

ህዝቦቿን ለዘመናት ጠፍሮ ከያዛቸው ድህነት በሂደት በማላቀቅና የላቀ
ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ በዓለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት
ከሚያስመዘግቡ ጥቂት ሀገሮች ተርታ ሀገሪቱ ለመሰለፍ እየጣረች ነው፡፡

ይህንኑ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አጠናክራ ለማስቀጠልና የጀመረችውን
የህዳሴ ጉዞ ይበልጥ ለማፋጠን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ
አዘጋጅታ ወደተግባር ከገባች ድፍን ሦስት የልማት መርሃ ግብር አመታትን
እያስቆጠረች ነው፡፡
ለልማቱ መቀላጠፍ ሀገሪቱ ቀደም ብላ ያልተማከለ አስተዳደርን መሰረት አድርጋ ከአዋቀረቻቸው ዘጠኝ ክልሎችና 2 የከተማ
አስተዳደሮች አንዱ በሆነው የአማራ ክልል የወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጅዎችን በመተግበር ለኢኮኖሚ ዕድገቱ የድርሻውን ማበርከት
ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

እንደሀገር በተጀመረው የልማት ጉዞ በክልሉ በሁሉም የልማት መስኮች ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ህዝቡ ለዘመናት ጠፍሮ
ከያዘው ድህነትና ኋላቀርነት ራሱን እያላቀቀና የሃብት ባለቤት እየሆነ በመጓዝ ላይ ይገኛል፡፡

የተጀመረውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥና የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካት ባለፈው ዓመት
በተከናወኑ የልማት ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አያሌው ጎበዜ ሰሞኑን ለክልሉ ምክር ቤት
10ኛ መደበኛ ጉባኤ ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡ በቀሪ የመርሃ ግብሩ ሁለት ዓመታትም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን
በሚፈለገው መልኩ ለማስቀጠልና የሚፈለገውን የዕድገት ምጣኔ ለማስመዝገብ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ርብርብ
እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይ በተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ዘርፍ በበጋ ወራት በተደራጀ የልማት ሰራዊት
በተከናወነው ስራ የተገኘውን መልካም ውጤት በሰብል ልማት ለመድገም በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራ ተከናውኖ ወደስራ መገባቱን
አስረድተዋል፡፡

ባለፈው የምርት ዘመንም ከመኽር አዝመራ የተገኘውን 80 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት በዘንድሮው መኽር ወደ 135 ሚሊዮን ኩንታል
ለማድረስና የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የእርሻና የዘር ስራው ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡
በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የክልሉ አርሶአደሮች በበጋ ወራት በምርት ጭማሪ ላይ አተኩሮ ስልጠና በመሰጠቱ በአሁኑ ሰዓት እንደ
በቆሎ፣ጤፍ፣ ስንዴና ሌሎች ሰብሎች ግብዓት በአግባቡ ተጠቅመው በመስመር በመዝራት ማልማት መጀመራቸውን አመልክተዋል፡፡ በቂ
የሆነ የግብዓት አቅርቦትና ስርጭት እየተከናወነ ሲሆን አዳዲስ አሰራሮችና ቴክኖሎጅዎችን አርሶአደሩ በመጠቀም የሚፈለገውን
የምርት ዕድገት ለማምጣት በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ባለሙያ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉን አርሶ አደር የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ባለፈው የበጋ ወራት በመስኖ ከለማው 620ሺህ ሄክታር መሬት በአንደኛና
ሁለተኛ ዙር እስካሁን ከ40 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል የሚበልጥ ምርት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡ በመስኖ ያገኘው የምርት መጠን ከመኽር
ካገኘው ምርት ጋር ሲነፃፀር ግማሽ ያህል መሆኑን አመልክተው ይህም የመስኖ ልማትን በሙሉ አቅም መፈጸም ቢቻል ዝናብ ሳንጠብቅ
በመኽር የሚገኘውን ምርት በመስኖ ማግኘት እንደሚቻል ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል፡፡ ክልሉ በመስኖ የመልማት አቅሙ ከፍተኛ
በመሆኑም በቀጣይ ልማቱን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠልና የግብርና ምርታማነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በበጋ ወራት
የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ አበረታች ውጤት የተመዘገበበት እንደነበር አቶ አያሌው ጠቁመዋል፡፡

በመሰረተ ልማት ዘርፍ በክልሉ መንግስት በጀት ምንጭ ከሚሰሩ የገጠር መንገዶች በተጨማሪ የቀበሌ ማዕከላትን ከዋና መንገዶች ጋር
ለማገናኘት እየተደረገ ያለው ስራ አርሶአደሩ ምርቱን በቀላሉ ወደ ገበያ አቅርቦ በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆን እያስቻሉ መሆኑን
ተናግረዋል፡፡

የመጠጥ ውሃ ለህዝቡ ለማዳረስ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን የተናገሩት አቶ አያሌው በአንዳንድ የውሃ ተቋማት
ግንባታ መጓተት የሚታይ በመሆኑ ተገቢ ትኩረት ሰጥቶ በማከናወን ለአገልግሎት በማብቃት ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል
ብለዋል፡፡ በ2007 በመጠጥ ውሃ ዘርፍ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ለማሳካት የክልሉን የመጠጥ ውሃ ሽፋን መቶ በመቶ ለማድረስ
መንግስት በየዓመቱ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የውሃ ተቋማትን በመገንባት ርብርብ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በከተሞች የሚስተዋለውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ በመንግስት ትልልቅ ፕሮጀክቶችና ሌሎች የስራ ዘርፎች ከ300 ሺህ
ለሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል እንዲሁም የትምህርት ፍትሃዊነት፣ ተደራሽነትና
ጥራትን በማረጋገጥ ረገድም በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ርዕሰ መስተዳደሩ ገልጸው የክልሉ መንግስት 163 ሚሊዮን በሚጠጋ
ወጭ ያሳተማቸውን ከ11 ሚሊዮን 632ሺህ በላይ የመማሪያ መጻፎች ማሰራጨቱንም አስታውቀዋል፡፡

የእናቶችና የህፃናት ሞትን ለመቀነስ እየተደረገ ላለው ጥረትም የጤና ጣቢያዎችን ቁጥር 859 የደረሰ ሲሆን ሆስፒታሎችን ደግሞ
ወደ74 ለማድረስ የ52 የመጀመሪያ ደረጃና የ3 ዞናል ተጨማሪ ሆስፒታሎች ግንባታ ስራ እየተፋጠነ መሆኑን አቶ አያለው
ተናግረዋል፡፡

በከተሞች የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ አዲሱን የሊዝ ስርዓት ተከትሎ ሲደረግ የቆየው ዝግጅት እየተጠናቀቀ በመሆኑ በቀጣይ
በሊዝና በምደባ በማህበር ለተደራጁና ለሌሎች አካላት እንደሚሰጥ አመልክተው ህገወጥ የቤት ግንባታም ስርዓት እንዲይዝ ይደረጋል
ብለዋል፡፡

በከተማና በገጠር በመሬት በግብር አከፋፈልና በሌሎች የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በያዝነው በጀት ዓመት ልዩ
ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ ለማፋጠንና ወደቀድሞ ገናናነቷ ለመመለስ
የጀመረችውን የልማት ግስጋሴ ለማፋጠን ምክር ቤቱ በአምስት ቀናት ቆይታው በተከናወኑ የልማት ተግባራትና በቀጣይ በሚከናወኑ
የልማት አቅጣጫዎች ላይ በጥልቀት መክሯል፡፡

ለክልሉ ልማት ማሳለጫም ምክር ቤቱ በ2006 በክልሉ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች ማስፈጸሚያ የሚሆን ከ18 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር
በላይ በጀት በማፅደቅ ጉባኤውን አጠናቋል፡፡