ህብረ ብሄራዊ አንድነታችንን ከሚንዱ ሃይሎች እንዲሁም ከጥንት ጀምሮ በሀይማኖቶች መካከል የነበረውን አብሮነት እሴታችንን የሚንዱ አሳሳቾችን በመከላከል አንድነታችንንና ኢትዮጵያዊ አብሮነታችንን በሚያጠናክክሩ አኩሪ እሴቶቻችን ላይ ማተኮር ይገባናል።
የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዶሃ

Saturday May 07, 2022

ህብረ ብሄራዊ አንድነታችንን ከሚንዱ ሃይሎች እንዲሁም ከጥንት ጀምሮ በሀይማኖቶች መካከል የነበረውን አብሮነት እሴታችንን የሚንዱ አሳሳቾችን በመከላከል አንድነታችንንና ኢትዮጵያዊ አብሮነታችንን በሚያጠናክክሩ አኩሪ እሴቶቻችን ላይ ማተኮር ይገባናል። በኳታር የኢፌዲሪ ኤምባሲ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፈይሰል በባህረ ሰላጤው አገራት የመጀመሪያ የሆነውና በ537 ስኩየር ሜትር በሚሸፍን መሬት ላይ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በሚጠይቅ ወጭ እየተገነባ ያለው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የዶሃ ጽርሃ አርያም ቅድሥት ሥላሴ ሕንጻ ግንባታው በመፋጠን ላይ ነው።


የዚሁ ህንጻ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅና ምዕመኑ አኩሪ አገራዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲቆይ ያስችላል በሚል ቤተ ክርስቲያኒቷ ያዘጋጀችው አውደ ትርኢት በትናንትናው እለት ተከፍቷል። በቤተክርስቲያኒቱ የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ አስተባባሪነት “ቤተክርስቲያንን እንወቅ፥ ቅጥሯንም እንገንባ” በሚል በተዘጋጀው በዚሁ ዐውደ ርዕይ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ መቀመጫቸውን በዶሃ ያደረጉ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ እንዲሁም የሩሲያ አምባሳደሮች እና ሌሎች ዲፕሎማቶች፣ የንግዱን ጨምሮ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተወከሉ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና በርካታ ቁጥር ያላቸው ምዕመናን ታድመውበታ።


በዚሁ አውድ ርዕይ ላይ የተገኙት በኳታር የኢፌዲሪ ኤምባሲ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፈይሰል አልይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያኒቷ በብዙ ፈተናዎች አልፋ የራሷን ህንጻ ገንብታ አገግልግሎቷን ለማስፋትና ኢትየዮጵያዊ አኩሪ እሴቶቿን በአከባቢው ላሉና ከተለያየ አለም ለተውጣጡ የውጭ አገር ዜጎች ለማስተዋወቅ እንድትችል የምታደርገው ጥረት )ከፍተኛ አድናቆትና አክብሮት የሚቸረው ነው ብለዋል። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አስቸጋሪው የስደት ህይወት ሳይበግራቸው አኩሪ አገራዊ እሴቶቻችንን ለተተኪው ትውልድ በማሸጋገር እና ለተቀረው አለም በማስተዋወቅ ሂደት ሚናቸውን በላቀ ደረጃ መወጣት እንዲችሉ የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የምታደርገው ጥረት እጅጉን የሚያኮራ ነው ያሉት አምባሳደር ፋይሰል ከምንም በላይ ቤተክርስቲያኒቷ ምዕመኑ እምነቱን ጠብቆ እንዲቆይ ከማስቻል ባሻገር ማህበረሰቡን በመገንባት ኢትዮጵያዊ እሴቶቻቸውን ለማጎልበት፣ ለበጎ አላማ መሰባሰብን እና መተባበርን ለመደገፍ፣ እንዲሁም ባህላዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን ጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት ማገዝ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ እና የኢትዮጵያ ወዳጅ ይጠበቃል ብለዋል።


ክቡር አምባሳደሩ በዚሁ መልዕክታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ታሪክ የገዘፈ ሚና ያላት መሆኑን በማስታወስ በተመሳሳይም በዶሃ የምትገኘው ዶሃ ጽርሃ አርያም ቅድሥት ሥላሴ ቤተክርስቲያንም በቀጠር ሚገኙ የዜጎቻችን ማህበራዊ መስተጋብራቸው እንዲጠናከር፣ ደህንነታቸው እንዲጠበቅና ወገናዊና አገራዊ አስተዋዕኦቸው እንዲጎለብት የምታደርገው ጥረት ከፍተኛ አድናቆት የሚቸረው ነው ብለዋል።


ቅድስት ቤተ ክርስቲቷም ሆነች ምዕመኖቿ ከኤምባሲው ጋር በቅንጅት በመስራት ለዜጎቻችን የሚሰጠውን አገልግሎት በማሳለጥ እና በመደገፍ እንዲሁም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ በተለያዩ አገራዊ የልማት አጀንዳዎችና ጥሪዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ አጋርነቷን በማሳየት ግንባር ቀደም ሚናዋን እንደተጫወተችው ሁሉ ይህንኑ ድጋፏን ማስቀጠል እንደሚጠበቅባትም አስገንዝበዋል። በዚህ ሂደት በአገር ቤትም ሆነ ከአገር ውጭ ባሉ አንዳንድ ጽንፈኛ ሃይሎች፣ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እና የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ የሚስተዋለውን በአገሪቱ የሃይማኖት ግጭት ያለ የማስመሰል እና ለረዥም ዘመናት ተጠብቆ የቆየውን ተከባብሮና ተደጋግፎ የመኖር አኩሪ እሴት የማጠልሸት እንቅስቃሴን ፍፁም ኢትዮጵያዊነትን ያልተላበሰ ስነ ምግባር እንድመሆኑ አጥብቀው ሊያወግዙት ይገባል ሲሉ መክረዋል።


ህብረ ብሄራዊ አንድነታችንን ከሚንዱ ሃይሎች እንዲሁም ከጥንት ጀምሮ በሀይማኖቶች መካከል የነበረውን አብሮነት እሴታችንን የሚንዱ አሳሳቾችን በመከላከል አንድነታችንንና ኢትዮጵያዊ አብሮነታችንን በሚያጠናክክሩ አኩሪ እሴቶቻችን ላይ ማተኮር ይገባናል በማለትም አጽንኦት ሰጥተው መክረዋል። ቤተ ክርስቲያኗ ይህንን ሕንጻ መገንባት እንድትችል ድጋፍ ላደረጉት የቀጠር አሚር ሼክ ተሚም ቢን ሃማድ አልታኒ፣ ለኢትዮጵያ መንግስትና የቤተ ክርስቲያኒቷ አስተዳዳሪዎች ምስጋና ያቀረቡት ክቡር አምባሳደር ፋይሰል መላው ኢትዮጵያዊ በተለይም በዶሃና አከባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በመተባበር የቤተ ክርስቲያኒቷን ህንጻ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።


በአውደ ርዕዩ ላይ ነዋሪነታቸውን በዶሃ ባደረጉ ሰዓሊያን የቀረቡ ስዕሎች ልዩ ልዩ የባህል አልባሳትና ጌጣጌጦች እና ሌሎችም አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን የኪነ ጥበብና እደ ጥበብ ስራዎች ለእይታ የቀረቡ ሲሆን ነዋሪነታቸው በዶሃ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ኤግዚቢሽኑን እንዲጎበኙት ተጋብዘዋል።