የኢትዮጵያ የውጪ ግንኙነት ከጥንት እስከ ዛሬ›› መጽሐፍ በይፋ ተመረቀ!

Thursday, 6 January 2022

መጽሐፉ ታኅሳስ 22/2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ዋና የመሰብሰቢያ አዳራሽ የመስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ፣ የደራሲው ወዳጅ ዘመዶችና አጋር ጓደኞች በተገኙበት በይፋ ተመርቋል፡፡

እኔም በተደረገልኝ የክብር ጥሪ በቦታው ተገኝቼ ለመመረቅና የወንድማችንም የደስታው ተካፋይ ለመሆን በመብቃቴ ደስ ብሎኛል፡፡ ወንድማችን አክሊሉ ይህንን የታላቅ እና ጥንታዊ ሀገር የውጪ ግንኙነት ታሪክ በመጻፍ ለአንባብያን አቅርቧል፡፡

እውነት ለመናገር ይህን ሰፊ አጀንዳ ለመጻፍ መነሳት ምን ያህል አርቆ አሳቢነት ፣ አንድ ዜጋ ለሀገሩ ማበርከት ካለበት በቁርጠኝነት የሚሰራው ብዙ ድካምን አስቦና ቆርጦ መነሳትን የሚጠይቅ እንዲሁም ባግባቡም ካልተሰራ ትችትን ሊያስነሳ የሚችል በመሆኑ የወንድማች አክሊሉ ፋና ወጊነት እጅጉን ሊያስመሰግነው የሚገባ ነውና እንኳን ደስ ያለህ ማለትን እፈልጋለው፡፡


በእኔ እይታ ይህን መጽሐፍ ትልቅ ዋጋ የሚያሰጡት ሦስት ነገሮች አሉ፡፡

#1.የመጀመሪያው የጸሐፊውን ማንነት ስንረዳነው፡፡ አክሊሉ በውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሃያ ዓመት በላይ የሰራ በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ዙሪያ የተሞክሮ ልምድ ፣ ዕውቀት እና ታሪክ የሚረዳ ዲፕሎማት ነው፡፡ በሀገረ ሕንድም ዲፕሎማት ሆኖ በሰራበት ወቅት ዲፕሎማት መሆንስ እንደ እርሱ ነው ያስባለ በጣም ጥሩ የሥራ ጊዜ እንደነበረው ሁላችንም ምስክር ነን፡፡ የኢትዮጵያን የውጪ ግንኙነት ታሪክ አንድ ሰው በጉዳዩ ላይ አንበብቦ ሊረዳ እና ሊጽፍ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሙያው በጉዳዩ ዙሪያ ላይ የሆነ ሰው ሲጽፍ ደግሞ በቂ የሆነ የመረጃ ምንጮችን በአግባቡ በማካተት ፣ በመተንተን እና ሊረሱ የሚችሉ አጀንዳዎችን በማካታት ለአንባብያን ምሉዕ የሆነ መረጃ መስጠት ይችላል፡፡


#2.በሁለተኛ ደረጃ አክሊሉ የሥነጽሑፍ ተሰጥኦ ያለው ሰው ነው፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹ ላይ ፣ በተለያዩ ማኅበራዊ መርሐግብሮች ላይ ወቅቶችን ያገናዘቡ ስነጽሑፎችን በማዘጋጀት በማቅረብ የምናውቀው ወንድማችን ነው፡፡ መጽሐፍን ለመጻፍ የሥነ ጽሑፍ ችሎታና ተሰጥኦ ያለው ሰው ሲገኝ ደግሞ ሥራውን ትልቅ ዋጋ እንድንሰጠው ያደርገናል፡፡ በሀገረ ሕንድ የአራት ዓመት የዲፕሎማትነት ሥራውን ሲያጠናቅቅ በሕንድ ያያቸውን መልካም ነገሮች ቀምሮ ‹‹#ይህችን_ሀገር_እንዳየኋት›› የሚል የመጀመሪያ መጽሐፉን አስመርቆ ለአንባብያን አቅርቦ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ከአራት ዓመት በኋላ ሌላ ሁለተኛ መጽሐፍን በይዘትም ፣ በጥልቀትም አዘጋጅቶ ብቅ ብሏል፡፡ በእውነቱ በጣምእናመሰግናለን፡፡ ከቀጣይ አራት ዓመታት ወይም ከዚያ በታች ደግሞ ሌላ ሦስተኛ ብንጠብቅስ እና ቃል ብናስገባውስ ምን ይመስላችኋል?


#3.በሦስተኛ ደረጃ መጽሐፉ ለአንባብያን የቀረበበት ወቅት መጽሐፉን ትልቅ ዋጋ እንድንሰጠው ያደርጋል፡፡ በዚህ ወቅት የሀገራችን የውጪ ግንኙነት ሥራ ወደ ተሸለ ደረጃ ለማደግ ጥረት እየተደረገበት ያለበትና ሀገራችንም በተለያ የውጪ ኃያላን ሀገራት በአንድም በሌላም ጫና እየተደረገባት ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የውጭ ግንኙነት ሥራው ዕውቀት መር ሊሆን የሚገባው ደረጃ ላይ በደረሰበት በዚህ ሰዓት የኢትዮጵያን የውጪ ግንኙነት ከጥንት እስከ ዛሬ ታሪክ በአንድ መድብል ሰንዶ ማዘጋጀት ትልቅ ዋጋ የሚያሰጥ ተግባር ነው፡፡ ብዙ የሀገራችን የታሪክ ምሁራን ፣ የውጭ ግንኙነት ባለሙያዎች ፣ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ተሰማርተው የሚሰሩ ባለሙያዎች ፣ የሀገራችን ዜጎች እና ሌሎችም ከመጽሐፉ ብዙ እንደሚጠቀሙ ተስፋ አደርጋለው፡፡ ይህን መጽሐፍ መሰረት አድርገው ብዙ ሌሎች መጽሐፎችን ለማዘጋጀትም እድልን እና መነሳሳትን ይፈጥራል፡፡


ማጠቃለያ ኢትዮጵያ ከ3000 ዓመት በላይ የሀገረ መንግስትነት ታሪክ ያላት ከቀደምት የዓለም ሥልጣኔ መካከል ቀድሞ ሥሟ የሚጠራ የአፍሪካ ኩራት የሆነች ሀገር ነች፡፡ ስለዚች ሀገር ብዙዎች አቅም በፈቀደ ደረጃ ታሪኳን ከትበዋል፤ ለቀጣይ ትውልድ እንዲሁም ለተቀረው ዓለም ማንነቷን ለማስረዳት ደክመዋል፡፡ አንድ ሰው ስለኢትዮጵያ ማወቅ ካለበት ሊረዳው የሚገባው ወሳኝ ጉዳይ ቢኖር አንዱ የሀገሪቱ #የውጪ_ግንኙነት_ታሪክ ነው፡፡ #ስለዚህ ሚዲያዎች ፣ የትምህርት ተቋማት እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙት ያላቸው መንግስታዊም ሆሉ የግል ተቋማት በመጽሐፉ ዙሪያ ለአንባብያን እንዲደርስ በማድረግ ፣ ውይይቶችን በማካሄድ ፣ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት እንዲሁም ዜጎች የሀገራቸው ታሪክ አንድ አካል የሆነውን የውጭ ግንኙነት ታሪክን እንዲያውቁ በማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ለማለት እወዳለው፡፡