የሰላሌ ኦሮሞ ባህላዊ እሴቶችን ለቱሪስት መስህብነት ለማዋል እየተሠራ ነው

January 25, 2022

/ኢዜአ/ የሰላሌ ኦሮሞ ባህላዊ የፈረስ ስፖርትን ጨምሮ ሌሎች ባህላዊ እሴቶችን በማጎልበት ለቱሪስት መስህብነት ለማዋል እየሰራ መሆኑን የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡


የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ጥናትና ምርምር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር እሸቱ ወንድሙ ለኢዜአ እንደገለጹት በሰላሌ ኦሮሞ አካባቢ በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች አሉ። ዩኒቨርሲቲው መስህቦቹን በዘመናዊ መንገድ በማዳበርና በማደራጀት ለቱሪዝም ልማት ለማዋል ካለፈው ዓመት ጀምሮ በጀት መድቦ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


የፈረስ ርባታና ባህላዊ የፈረስ ውድድርን ከአካባቢው ወግና ልማድ ጋር አጣጥሞ የቱሪስት መስህብ ለማድረግ ከግንባታ በተጨማሪ የጥናትና የምርምር ሥራዎች እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


ዩኒቨርሲቲው ከውጫሌ ወረዳ በተረከበው 14 ሄክታር መሬት ላይ የተደራጀ የፈረስ ስፖርት ማዕከልና የመሮጫ ሜዳ ግንባታ መጀመሩን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ማዕከሉ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የፈረስ ዝርያዎችን በጥናት በመምረጥና በማስተዋወቅ ለትርኢትና ለውድድር ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። ባህላዊና ዘመናዊ የፈረስ እንክብካቤ፣ አረባብና ስፖርታዊ ጨዋታዎችን ከአካባቢው ባህል ጋር በማዛመድ ለጎብኝዎች መዝናኛነት በማዋል ገቢ ለማግኘት እየተሰራ ነው ብለዋል።


በሌላ በኩል በአካባቢው በሃይማኖታዊና ባህላዊ ሁኔታ የሚዘወተሩ ትዕይንቶችንና ተያያዥነት ያላቸው ሁነቶችን አጥንቶ ለቱሪዝም ልማት ለማዋል እየተሰራ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡


“ወደፊት በምርምር ውጤት በመመሥረት ከዞኑ አስተዳደር ጋር በመተባበር ወደ ድርጊት መርሃ ግብር ይገባል” ብለዋል፡፡ እንደ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ እያከናወነ ያለው ስራ የአገሪቱን የቱሪዝም ልማት ይደግፋል፡፡ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሜሮን መኮንን በአካባቢው በአዘቦትና በበዓላት የሚዘወተሩ የፈረስ ገና ጨዋታ፣ የፈረስ ጉግስ፣ ሸርጥና ትርዒቶች የመዝናኛ ይዘት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡


የቱሪዝም ሃብቶቹ ገቢን የሚያሳድጉ በመሆናቸው ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው በባህላዊ የፈረስ ውድድር የሚታወቁት አቶ አብርሃም ታደሰ ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ባህልና ወግ መሰረት በማድረግ የጀመረው ጥረት የፈረስ ባህላዊ ጨዋታ እንዳይረሳ ያደርጋል ብለዋል።