የአፍሪካዊያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አጋርነት ባይኖር ኖሮ እንደ ሀገር አደጋ ውስጥ እንወድቅ ነበር
የአፍሪካዊያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አጋርነት ባይኖር ኖሮ እንደ ሀገር አደጋ ውስጥ እንወድቅ ነበር
- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

February 5, 2022

የአፍሪካዊያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አጋርነት ባይኖር ኖሮ ኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት በገጠማት ችግር ምክንያት እንደ ሀገር አደጋ ውስጥ ትወድቅ ነበር አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ሲጀመር በመክፈቻው ላይ ባሰሙት ንግግር፥ ያለፈው አንድ ዓመት ለኢትዮጵያ ከባድ እንደነበር አመልክተዋል።


ሀገሪቱ ያጋጠማት ፈተና የውስጥ እና ህግና ስርዓትን የማስፈን ጉዳይ ቢሆንም፥ የውጭ አካላት ሚና ግን ችግሩን ከባድ እንዳደረገው ነው የተናገሩት። በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ አፍሪካዊያን ወንድሞች እና እህቶች የኢትዮጵያን እውነት በመረዳት እና በመደገፍ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆማቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላማዊ መንገድ አማራጭ በመስጠት የተናጥል የተኩስ አቁም በማድረግ በህግ ማስከበር ስራ ላይ የነበሩት ወታደሮችን ከግጭት አካባቢዎች ማውጣቱን ገልፀዋል።


እስረኞችን በመፍታትም ለሰላም ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር መስራቱንም ነው ያመለከቱት። ለሰላም የማንፈነቅለው ድንጋይ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በሀገሪቱ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙን ተናግረዋል። ይህ የመንግስት ጥረት እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወቅታዊውን የዓለም እውነታ ባገናዘበ መልኩ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ አንስተዋል።


የአፍሪካ ድምፅ በዓለም መድረክ በደምብ ሊደመጥ ይግባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አፍሪካ በአግባቡ በምትወከልበት አግባብ እንዲሻሻል መጠየቃችንን ልንቀጥል ይግባል ብለዋል። ከዚህ በፊት በተደረሰው ስምምነት መሰረት በፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ሁለት ቋሚ መቀመጫ እና አምስት ተለዋጭ መቀመጫ እንዲኖራት ግፊት ማድረግ አለብን ነው ያሉት። ስለ አፍሪካ የተሳሳተ ምስል በሚፈጥሩ እና አፍሪካዊያን ሳይቀሩ ስለ ራሳቸው የተሳሳተ አመለካከት እንዲጨብጡ የሚያደርጉ የመገናኛ ብዙሃን የሞሉበትን የዓለም የሚዲያ ምህዳርን መቀየር እንደሚገባ ተናግረዋል።


ለዚህም ፓን አፍሪካዊ የሚዲያ ተቋም በማቋቋም ስለ አፍሪካ የተያዘውን የተሳሳተ ትርክትን ልናርም እና አፍሪካ ስለራሷ ለዓለም ልትናገር ይግባል ብለዋል። የኮቪድ-19 አሉታዊ ጫና ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ፈተና ሆኖ በቀጠለበት በዚህ ወቅት በአህጉሪቱ የምግብ ዋስትና ችግር በ60 በመቶ ማደጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፀዋል። ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የበረሃ አንበጣ ወረርሽን እና ሌሎች የዓየር ንብረት ለውጥ ያመጣቸው ችግሮችም ለአፍሪካ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ ፈተና መሆናቸውን በንግግራቸው ተመልክቷል። ኢትዮጵያ በተለይም ከአካባቢ መራቆት ጋር ተያይዞ እየገጠማት ያለውን ፈተና ለመቋቋም በአራት አመት ውስጥ 20 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል አቅዳ እንደነበር ጠቅሰዋል።


በሶስት ዓመታት ውስጥ 18 ቢሊየን ችግኝ መተከሉ፤ አራተኛው አመት ላይ የተተከለውን ችግኝ 25 ቢሊየን ለማድረስ መታቀዱን አስታውቀዋል።