1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 21 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን እና በደቡብ ክልል ሰገን ህዝቦች ዞን አማሮ
ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት እንዲከሰት ያደረጉ አካላትን ለህግ የማቅረብ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።

ሀምሌ 16 እና 19 ቀን 2009 ዓ.ም በኮሬ ብሔረሰብና በጉጂ ኦሮሞ መካከል በተከሰተው ግጭት በሰውና በንብረት
ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

ከሁለቱም ወገኖች በኩል የ13 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፥ ቤታቸው የተቃጠለባቸውና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው
መኖራቸውም ተጠቅሷል።

በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ የሰጡት የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ፥ በአሁኑ
ጊዜ ሁለቱ ክልሎች ችግሩን ለመፍታት በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

የኦሮሚያ ክልል እና የደቡብ ክልል የፀጥታ ሀይሎች በጋራ በሰሩት ስራም በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው ግጭት መረጋጋቱን
አቶ አዲሱ አስታውቀዋል።

ግጭቱ እንዲከሰት ያደረጉ አካላትን ለህግ የማቅረብ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ሃላፊው ገልፀዋል።

የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይሉ በበኩላቸው፥ በደቡብ ክልል ሰገን
ህዝቦች ዞን አማሮ ወረዳ እና በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ግጭት መረጋጋቱን
ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የግጭቱን መንስኤ የሚያጣራ ግብረኃይል ወደ ስፍራው መላኩንም ሃላፊው ገልፀዋል።

ቀደም ሲል በሁለቱ አካላት መካከል ከወሰን ጋር በተያያዘና በግጦሽ ምክንያት ተመሳሳይ ግጭት ይከሰት እንደነበርም
አስታውሰዋል፡፡

በአዋሳኝና አጎራባች አካባቢዎች የግጭት መንስኤ የሆኑ አስተዳደራዊ ውሳኔን የሚፈልጉ የወሰን ጉዳዮችን ለመፍታትና
ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር በመነጋገር እየተሰራ መሆኑንም
ጠቅሰዋል።

ሃላፊው አያይዘውም ግጭቱ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በመቆሙ ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋሙ ሥራ በሁለቱም ክልሎች
በኩል በተቀናጀ ጥረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በግጭቱ እጃቸው ይኖርበታል ተብለው የሚጠረጠሩ ፀረ ሰላም ኃይሎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ለህግ የማቅረብ ሥራ
ይሰራል ነው ያሉት።

ተጨማሪ መረጃ፥ ከኢዜአ
admin@hebrezema.info
1