1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
admin@hebrezema.info
ጥልቅ ተሀድሶው ጠልቆ መርምሮ ይሆን?
January 14, 2017
በኢህአዴግና በአጋር ድርጅቶቹ የተጀመረው ጥልቅ የተሀድሶ ንቅናቄ መላው የህብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተና የማደስ አቅምም እንዳለው ይጠበቃል፡፡
ይህ ሂደት ፓርቲው የገጠሙትን የተዛቡ የአስተሳሰብ ዝንባሌዎችና ጉድለቶችን ለመሙላት የሚያስችልና ከልቡ ለመታደስ ለቆረጠ አመቺ ጊዜ አሁን
መሆኑን አመላካች ነው፡፡

መታደስ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የማጥራት ሥራ ሲሆን፤ “በጥልቀት መታደስ ማለት ደግሞ ከነበረው ችግር ለመላቀቅ ወይም ነፃ ለመውጣት ስር
ነቀል ርምጃ መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል። በተሀድሶ የሚታወቀው ኢህአዴግ አሁን ያሉበትን ችግሮች መሰረታዊ መንስኤዎቻቸውን በመለየት መዋቅራዊ፣
ድርጅታዊና መንግሥታዊ እንቅፋቶችን ለመቅረፍ በሚያስችል መልኩ ለመሥራት ቆርጦ የተነሳበት ወቅት ላይ መሆኑንም ያመላክታል፡፡

ኢህአዴግ መጀመሪያ ባጋጠመው ችግር ውስጡን ሲፈትሽ በተሀድሶ ያካተታቸው ነጥቦች በዝርዝር ተቀምጠው ነበር፤ ከግምገማው በኋላም መልካም
ጅምሮች ቢኖሩም አጥጋቢ ውጤት ባለመታየቱ መንግሥት ለሁለተኛ ጊዜ ተሀድሶ ውስጥ ለመግባት ተገድዷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአገር አቀፍ ደረጃ
የጥልቅ ተሀድሶው አካል የሆኑ ውይይቶች መደረጋቸው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት እና መሰል ችግሮችን ለመፍታት የማጥራት ሥራ
በመሥራት ላይ የሚገኘው ኢህአዴግ የጥልቅ ተሀድሶው የተገቢነት መንፈስ በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ተደራሽነቱን ማስፋት
ይጠበቅበታል።

የሕዝብ የልማት ተሳትፎ ማነስ፣ በመልሶ ማልማት ፈጥኖ መገንባት ላይ ያሉ ጉድለቶች፣ በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታ መጓተት፣ የከተማ ጽዳት
ብልሹነት፣ የትራንስፖርት ችግሮች ወዘተ...) ከዚህም በላይ በሌሎች ክልሎች እንደታየው ሕዝቡ በቁጣ ገንፍሎ አይውጣ እንጂ ቀላል የማይባል
ምሬትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት እንዳለ በግልፅ ይታወቃል፡፡ በኢፍትሐዊነት፣ በሙስናና ብልሹ አሠራር፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት ማጣትና ሥርዓት
አልበኝነት ክስተት አሁን ያለው አመራር ውጤት መሆኑ እየተገለፀ ነው፡፡

ሕዝቡን ሲበድሉና ሲያማርሩ የነበሩ ኃላፊዎች አሁንም በአመራርነት እርከን ላይ እንዳይቀመጡ ማድረግ፣ የተጀመረውን ዴሞክራሲ ከማስቀጠል ብሎም
ዜጎችንና ንብረትን ከአደጋ ለመታደግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡ ለመልካም አስተዳደር እንቅፋት የሆኑ አሠራሮች እንዲወገዱ ከታሰበ ሕዝብና
መንግሥት ተቀራርበው የሚነጋገሩበት መድረክ መፈጠር፣ እሮሮ የሚያስነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ፣ የአመራር አባላት በስብስባና
በተለያዩ ምክንያቶች ጊዜያቸውን ከማባከን ባለፈ ወደ ሕብረተሰቡ ወርደው ችግሩን እንዲመለከቱ ማድረግ የግድ ወሳኝ ሥራ ነው፡፡
በከተማዋ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ተገልጋዩን ቀርቶ ራሱን ሠራተኛውን የሚያማርሩ አሠራሮች ትንሽ አይደሉም፡፡ በቅጥር፣ በዝውውር፣ በምደባና
በሹመት ላይ የሚታየው ደባ ኢህአዴግን ሰው እንዲጠላ የሚያደርግ ነው፡፡ ቅሬታ ሰሚ፣ የዲሲፕሊን ኮሚቴ፣ የመልካም አስተዳደር ወዘተ... የሚሉ
አወቃቀሮች የይስሙላ ናቸው የሚሉ በርካታ እሮሮዎች ይደመጣሉ፡፡

መንግሥት ችግሩ ጥልቅ ተሀድሶ እንደሚያስፈልገው አምኗል። የአገራችንን ሕዝብና መንግሥት አደጋ የደቀነ ጉዳይ እንደሆነ በማመኑም ሕብረተሰቡ
በደንብ ተረድቶት በጋራ ከችግሩ የምንወጣበትን መስመር መዘርጋት አለብን» በማለት ምላሽ ሰጥቷል። ይሁን እንጂ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች
ግምገማ እየተጠናቀቀ ነው መባሉ በርግጥ ጥልቅ ተሀድሶው ጠልቆ መርምሮ ይሆን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ እነኛ በኔትወርክና በቡድንተኝነት የተዘፈቁ፣
የሕዝብ መሬት ያዘረፉና የድርሻቸውን የወሰዱ፣ በኪራይ ሰብሳቢው ባለሀብት የሆኑ፣ የውጭ ጉዞን የውሃ መንገድ ያደረጉ፣ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ
ፊንፊኔ ዙሪያ በርካታ ቤቶች እያሉዋቸው በመንግሥት ቤት የሚኖሩ፣ ከመንግሥት ሥራቸው ሌላ ነጋዴ የሆኑ በምን ሁኔታ ተፈትሸው ይሆን?

addiszemen
1