1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
ኢሕአዴግና አገር አቀፍ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያቋረጡትን ድርድር ጀመሩ
May 31, 2018
ነአምን አሸናፊ
ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ የተቋረጠው የገዥው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር
(ኢሕአዴግ) እና 15 አገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቱ ምርጫ፣ ተያያዥ ሕጎችና አዋጆች ላይ
የሚደረገው ድርድር እንደገና ተጀመረ፡፡

ጥር 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ኢሕአዴግና 15 አገር አቀፍ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በድርድሩ አራተኛ አጀንዳ በሆነው የፀረ
ሽብርተኝነት አዋጅ 652/2001 ላይ የሚያደርጉትን ድርድር መቋጨት ባለመቻላቸው፣ ድርድሩ በይደር እንዲቆይ
መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡

ሆኖም ረቡዕ ግንቦት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. በይደር በቆየው በፀረ ሽብር ሕጉና በብሔራዊ መግባባት አጀንዳ ላይ
ድርድሩ እንደሚቀጥል፣ የድርድሩ ምክትል አደራዳሪ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡

ምንም እንኳን ብሔራዊ መግባባት የሚለው የድርድሩ የመጨረሻ አጀንዳ የነበረ ቢሆንም፣ ፓርቲዎቹ ባደረጉት
ኢመደበኛ ውይይት ወደ አምስተኛ አጀንዳነት እንዲመጣ በመወሰኑ ድርድሩም በዚህ መሠረት እንደሚካሄድ አክለው
ገልጸዋል፡፡

በጥር ወር ተካሂዶ በነበረው ድርድር ላይ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን አስመልክቶ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአብዛኛው
ያቀረቡት የድርድር ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ፣ ኢሕአዴግ ምላሹን እስኪሰጥ ድረስ ድርድሩ በይደር እንዲቆይ የ11
ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ በይደር እንዲቆይ ጠይቆ እንደነበር፣ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ሊቀመንበር
አቶ ትዕግሥቱ አወሉ አስታውሰዋል፡፡

በወቅቱ ኢሕአዴግን ወክለው እየተደራደሩ የነበሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ‹‹ያነሳችሁት ሐሳብ የሕግ ዕውቀት
የሚጠይቅ በመሆኑ የሕግ ባለሙያዎች ዝርዝሩን እስኪያቀርቡ ድረስ፣ በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ውይይቱን
እንቀጥል፤›› ማለታቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡

በዚህም መሠረት ረቡዕ ግንቦት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሚቀርበው ብሔራዊ መግባባት አጀንዳ በተጨማሪ፣ በፀረ
ሽብርተኝነት አዋጁ ላይ የኢሕአዴግን ምላሽ እንደሚያዳምጡ አቶ ትዕግሥቱ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በተደረጉት የገዥው ፓርቲና አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ
ቁጥር 573/2003 እና የተሻሻለውን የኢትዮጵያ የምርጫ አዋጅ ቁጥር 532/993 ለማሻሻል መስማማታቸው
የሚታወስ ነው፡፡

ethiopianreporter.com
admin@hebrezema.info
1