1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
በስደት ምክንያት ከኢትዮጵያ ወጥተው በሳዑዲ ዓረቢያ፣ በግብፅና በሊባኖስ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን፣ ከፍተኛ
የአካል ጉዳት እየደረሰባቸው በግድ እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑ ታወቀ፡፡

ከሳዑዲ ዓረቢያ ተመላሾች የአቀባበልና አሸኛኘት ኮሚቴ አባልና የብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ሥጋት አመራር ኮሚሽን
ተወካይ አቶ አስመላሽ ገብረ ሕይወት ሐሙስ ሐምሌ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ
እንደተናገሩት፣ ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ብቻ ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 3,653
ኢትዮጵያዊያን ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ግብፅና፣ ሊባኖስ በግድ እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከልም አንዳንዶች
እጃቸውና እግራቸው ተሰብሮ የመጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ይህን ያህል መጠን ያላቸው ኢትዮጵያዊያን በግድ ከዓረብ አገሮች እንዲወጡና ከፍተኛ
እንግልት እንዲደርስባቸው መደረጉን የገለጹት አቶ አስመላሽ፣ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያዊያን ከሳዑዲ ዓረቢያ የሚመጡ
መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ሳዑዲ ዓረቢያ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች እንዲወጡ ከማወጇ
በፊት፣ ታስረውና ሕገወጥ ተብለው ተይዘው የነበሩ ኢትዮጵያዊያን በግድ እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ታስረው የሚመጡ ዜጎች ጫማ እንኳን የሌላቸውና ከፍተኛ የሆነ የሞራልና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑንም
ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከእነዚህ የዓረብ አገሮች በግድ የሚመጡ ዜጎችን መንግሥት እየተቀበለና ወደየመጡበት አካባቢ እየመለሰ እንደሚገኝም
ተወካዩ አስረድተዋል፡፡ እነዚህ በግድ እንዲወጡ የሚደረጉ ዜጎች ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሲደርሱ ብሔራዊ የአደጋ
መከላከልና ሥጋት አመራር ኮሚሽን ተቀብሎ ብርድ ልብስ፣ ብስኩትና ውኃ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሰጠችው ተጨማሪ አንድ ወር ከተጠናቀቀ በኋላ
ይህ ችግር እየባሰ እንደሄደ አክለዋል፡፡ ከአዋጁ መጠናቀቅ በኋላም የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ቤት ለቤት በማሰስና
በመያዝ ወደ ኢትዮጵያ በግድ እንደሚመልሳቸው ተመላሾች ገልጸዋል፡፡ ንብረት ይዘው እንደማይወጡና በተደጋጋሚ
አሻራ ተነስተው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚላኩ አስረድተዋል፡፡
admin@hebrezema.info
1