1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከአምቦ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ጋር ነገ
ይወያያሉ
April 10, 2018
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከአምቦ
ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ጋር በነገው እለት ይወያያሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ለመወያየት እና የስራ ጉብኝት ለማድረግ ነገ አምቦ የሚገቡ
ሲሆን፥ በርካታ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ወደ አምቦ እንደሚያቀኑም ተነግሯል።

በነገው እለት ጠዋት በአምቦ ከተማ ስታዲየም በሚካሄደው ዝግጅት ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ
ተገኝተው ለአምቦ ከተማ እና አካባቢው ነዋሪዎች በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ንግግር የሚያደርጉ መሆኑም ተነግሯል።

በተጨማሪም በቀጣይ ሊደረጉ በሚገቡ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ መእክቶችንም እንደሚያስተላልፉም ተነግሯል።

በአምቦ ከተማ ስታዲየም በሚደረገው ዝግጅት ላይም ቁጥራቸው እስከ 30 ሺህ የሚደርሱ የአምቦ ከተማ እና አካባቢው
ነዋሪዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

የአምቦ ከተማ ከንቲባ አቶ በሪሶ አመኖ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ
አምቦ ከተማ መምጣታቸው የህዝቡ የጋራ መግባባት እና አንድነትን ለማነሳሳት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በነገው እለት ወደ አምቦ ከተማ የሚጓዙትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ለመቀበል ዝግጅት
መጠናቀቁንም ገልፀዋል።

የአምቦ ከተማ ነዋሪዎችም ያለገደብ በአምቦ ስታዲየም በሚካሄደው መርሃ ግብር ላይ መሳተፍ ይችላሉ ሲሉም
ተናግረዋል።

የምእራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ማሾ ኦላኒ በበኩላቸው፥ በነገው እለት በአምቦ ከተማ በሚካሄደው ዝግጅት ላይ
በምእራብ ሸዋ ዞን ከሚገኙ 22 ወረዳዎች የተወጣጡ የህዝብ ተወካዮች እንደሚሳተፉ ገልፀዋል።

በሰርካለም ጌታቸው
admin@hebrezema.info
1