1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በዓለም ዓቀፍ የመገናኛ ብዙሃን እይታ
April 24, 2018
    ሃብታሙ አክሊሉ(ኢዜአ)

‘‘ስንደመር እንጠነክራለን’’ በሚል ፍልስፍና የሚታወቁት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ በዛሬው
ዕለት ሃላፊነቱ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ፀድቆላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት የኢትዮዽያ ህዝቦች
አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ሊቀመንበር ሆነው ከተመረጡበት ጊዜ አንስቶ በርካታ የሃገር ውስጥና
የውጭ መገናኛ ብዙሃን የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ሊረከቡ እንደሚችሉ በሙሉ እምነት ሲዘግቡ ቆይተዋል። መገናኛ
ብዙሃኑ እንዳሰቡት ሆኖ ዶ/ር አቢይ አህመድ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሃላፊነቱን ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር
ሃይለማርያም ደሳለኝ እጅ ተረክበው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል። በፓርላማው ታሪክም አይረሴ የስልጣን ርክክብ ንግግርም
አድርገዋል።

ይህንንም አስመልክተው የሃገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃን በየዘገባዎቻቸው ፊት ለፊት የተለያዩ መረጃዎቻቸውን
ይዘው ወጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ለኤርትራ መንግስት የሰላም ጥሪ አቀረቡ በማለት ከሁሉ
የቀደመ መረጃውን ይዞ የወጣው ቢቢሲ ነው። በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ አገራት ህዝቦች የጋራ
ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት ዝግጁነቱ እንዳላቸው የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኤርትራ
መንግስትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ ጥሪ ማቅረባቸውንም ቢቢሲ የዳሰሰው ጉዳይ ነው።

የኢትዮዽያ ፓርላማ ዶ/ር አቢይ አህመድን የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እንዲያገለግሉ ቃለ መሃላቸውን ተቀበለ
በሚል ዘገባውን የጀመረው የሬውተርስ የዜና ወኪል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ማሻሻያዎችን ተፈፃሚ
እንደሚያደርጉ እምነት እንደተጣለባቸው አስነብቧል። የዜና ወኪሉ አያይዞም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ዕለቱ
ለሰለማዊ የስልጣን ርክክብ ምስክር የምንሆንበት ታሪካዊ ቀን መሆኑን የጠቀሱበትን እንዲሁም አሁን ሃገሪቷ ያለችበት
ሁኔታ ዕድልንም ስጋትንም ይዞ እንደቀረበ መግለፃቸውን አንስቷል።

የኢትዮዽያ ምክር ቤት ወጣትና አንደበተ ርቱዕ አብይ አህመድን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ሰየመ በሚል መልዕክት
ዘገባውን ያሰራጨው የአሶሾየትድ ፕሬስ ዘጋቢ ከአህጉሪቱ በህዝብ ብዛት በሁለተኛነት የተቀመጠችውን ሀገር ወደ ሰላም
ጎዳና እንደሚመራት መታመኑን አስነብቧል። በተቃውሞ ወቅት ለጠፋው ህይወት ይቅርታ የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ
በአስተዳደራቸው ዘመን ቅሬታዎችን እና አለመግባባቶችን ከሃይል ይልቅ በውይይት ለመፍታት እንደሚጥሩ
መናገራቸውንም ዜና ወኪሉ ዘግቧል። ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰፊ ዕድሎችን ለማመቻቸት ብሎም ሙስናን በመዋጋት የህግ
የበላይነትን ለማክበር ቃል መግባታቸውንም አሶሺየትድ ፕሬስ በዘገባው አክሏል።

በስልጣን ርክክብ ንግግራቸው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ በሃገር ውስጥም ሆነ ውጭ ሃገር የሚገኙ
ኢትዮዽያውያን በጉጉት ሊያደምጡት የሚችሉትን ንግግር ማድረጋቸውን በዘገባው መጀመሪያ ያነሳው አዲስ ስታንዳርድ
ለኩሩ ሃገራቸው ህልውና ሲዋደቁ ለተሰዉ ሰማዕታት ፀሎት ከተደረገ በኋላ የስልጣን ርክክብ ፕሮግራሙ መጀመሩን
ተናግሯል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቃውሞ ለጠፋው ህይወት ይቅርታ ከመጠየቅ ለኤርትራ መንግስት የሰላም ጥሪን
እሰከማድረግ የዘለቀ ሰፊ ንግግር ማድረጋቸውንም መረጃው አልሸሸገም።

በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በተቀሰቀሱ ሰፊ ግጭቶች የሰው ህይወት ዋጋን በማስከፈሉ ባለፈው የካቲት ወር አጋማሽ ላይ
በይፋ ስልጣናቸውን በለቀቁት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ምትክ የኢትዮዽያ ፓርላማ ዶ/ር አቢይ
አህመድን አዲሱ የኢትዮዽያ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መሰየሙን የዘገበው ዋሺንግተን ፖስት አዲሱ ጠቅላይ
ሚኒስትር ካለፈው ስህተቶቻችን በመማር ስህተቶቹንም በአስቸኳይ መፍታት እንደሚገባ መናገራቸውን አስከትሎ ፅፏል።
አዲሱ መሪ ከኤርትራም ሆነ በውጭ ከሚኖሩ የዲያስፖራ ማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ተቀራርቦ ለመነጋገር ዕቅድ እንደያዙም
ዘገባው አያይዞ አቅርቧል።

በአዲሱ መሪ ቀጣይ ሀላፊነት ዙሪያ የተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦችና ፖለቲከኞችን አስተያየት ይዞ የወጣው የዋሺንግተን ፖስት
ዘገባ ታዋቂው ፖለቲከኛ መረራ ጉዲና የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የቀጣይ የስራ ዕቅድን ወክሎት በተወዳደረው ፓርቲ
ፈቃድ ላይ ሊመሰረት እንደሚችል የሰጡትን አስተያየት አስነበቧል። ታዋቂው የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት
አትሌት ሃይሌ ገ/ስላሴ በበኩሉ የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫ ለበርካታ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጥ
እንደሚችል እምነቱ እንደሆነ መግለፁን እንዲሁ ጋዜጣው በእትሙ አስነብቧል።

በፓርቲው የ27 አመታት የገዢነት ዘመን ዶ/ር አቢይ አህመድ ከኦሮሞ ብሄረሰብ የተገኘ የመጀመሪያው ጠቅላይ
ሚኒስትር መሆኑን ያስነበበው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በውጭ ሃገር ለሚኖሩ ዳያስፖራ ፖለቲከኞች የይቅርታ
መልዕክታቸውን ከልብ በመነጨ ስሜት ማቅረባቸውን ዘግቧል። ልክ እንደሌሎቹ መገናኛ ብዙሃን ሁሉ ኤ ኤፍ ፒም
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቃውሞ እንቅስቃሴ ወቅት ለጠፋው የንፁሃን ህይወት ይቅርታ መጠየቃቸውን አፅንኦት ሰጥቶታል።

ዴይሊ ሜይል የተሰኘው ድረ-ገፅ በዘገባው መካከል አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከበፊቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰንደቅ አላማና
ህገ መንግስቱን መረከባቸውን አስነብቦ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደ ጠላት ሳይሆን ለሃገር የተለየ አማራጭን ሊያመጡ
እንሚጥሩ ወንድሞች እንደሚቆጥሯቸው መናገራቸውን ዋቢ አድርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ስለ አስቸኳይ
ጊዜ አዋጁ ምንም አለማለታቸውንም ዴይሊ ሜይል ይዞ ወጥቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃገሪቱ ሰፍኖ የቆየውን ሙስና ለማስወገድ ጥረት እንደሚያደርጉ መግለፃቸውን በማስቀደም
የዘገበው አፍሪካ ኒውስ አስተዳደራቸው ትርጉም ያላቸው ፖሊሲዎችን ተግባራዊ በማድረግ የትምህርት ጥራትን
ለማምጣት እንደሚሰራ መግለፃቸውን አስነብቧል። ለወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድሎችን ለማመቻቸት እንደሚሰሩ ብሎም
ወጣት የንግድ ፈጠራና የቢዝነስ ሰዎችን ለመፍጠር እንደሚሰራም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ዋቢ ባደረገው ዘገባ አፍሪካ
ኒውስ ጠቁሟል።

የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሃላፊነት መምጣት በዘገባዎቻቸው የዳሰሱት መገናኛ ብዙሃንም ሆኑ ሌሎች የማህበራዊ
ትስስር ድረ-ገፆች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣን ርክክብ ወቅት ያደረጉት ንግግር ፍሬ ሃሳቦችን አንዳችም ሳያስቀሩ
የዘገባዎቻቸው አካል አድረገዋቸዋል፤ እያደረጓቸውም ይገኛሉ።
admin@hebrezema.info
1