1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
የህዝብ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ግጭትን ማስቆም እንጅ ማባባስ የለበትም!  

የሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ እና የቢሮ ሃላፊው "ግጭትን የሚያባብሱ መረጃዎች" ከመልቀቅ እንዲቆጠቡ ከፌደራል መንግስት ማስጠንቀቂያ
ተሰጣቸው
October 9, 2017
በኮሙኒኬሽንና መገናኛ ብዙሃን አካላት የሚወጡት መረጃዎች በህዝቦች ሰላምና አንድነት ላይ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል

አዲስ አበባ መስከረም 28/2010 በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት በተመለከተ የኮሙኒኬሽንና መገናኛ
ብዙሃን አካላት የሚወጡ መረጃዎች በሁለቱ ህዝቦች ሰላምና አንድነት ላይ ብቻ ትኩረት የሚያደርግና ለተፈጠረው ችግር መቃለል ገንቢ ሚና የሚጫወቱ
መሆን እንዳለባቸው መንግስት አሳሰበ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዛሬ ማምሻውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልገሎት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በሁለቱ ክልሎች መካከል
የተፈጠረውን ግጭት የሚያባብሱና ህዝቡን ጥርጣሬ ላይ የሚጥሉ መረጃዎች እየተሰራጩ ናቸው።

እነዚህ መረጃዎች በምንም ዓይነት መልኩ የየትኛውንም ክልል መንግሥት፣ አመራር አባላት፣ የአገር ሽማግሌዎች ብሎም የየክልሎቹን ህዝቦች ፍላጎት
ይወክላል ብሎ መንግሥት በፍጹም እንደማያምን መግለጫው አብራርቷል።

የኮሙዩኒኬሽን እና የመገናኛ ብዙሃን አካላት የተፈጠረውን ግጭት የሚያባብሱ መረጃ ከመልቀቅና ለዘገባዎቹ የአጸፋ ምላሽ ከመስጠት እንዲታቀቡ
ያመለከተው መግለጫው፤ እነዚሁ አካላት ካለባቸው አገራዊ ተልዕኮ እንዲሁም ግጭቱን አስመልክቶ መንግሥት በቅርቡ ከሰጠው አቅጣጫ አኳያ ለሁለቱ
ህዝቦች ሰላምና አንድነት በሚጠቅሙ መረጃዎች ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ አሳስቧል።

በተለይም ለተፈጠረው ችግር መቃለል የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ መንግሥት በድጋሚ ጥሪውን አቅርቧል።

በአሁኑ ወቅት ከኮሙኒኬሽንና የመገናኛ ብዙሃን አካላት የሚወጡ መረጃዎች የመንግስትን አቅጣጫና ፍላጎት የሚቃረኑ መሆናቸውን ያስታወሰው
መግለጫው፤ በተለይ መስከረም 23 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ድረ-ገፅ እና የቢሮ ኃላፊ ፌስቡክ ገጽ  ላይ "
የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል መንግስትና አገር ሽማግሎች በኦሮሚያ ጥቃት ላይ የጋራ አቋም መግለጫ ይፋ አደረጉ" በሚል ርዕስ የተሰራጨው መረጃ መንግሥት
ያስቀመጠውን አቅጣጫ የሚቃረን መሆኑን አብራርቷል።

ከኢትዮጵያ ሶማሊ ሰላም ወዳድ ህዝብ እና መንግሥት እንዲሁም የፌዴራል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ከሚያራምድ ማንኛውም አመራር የማይጠበቅ መሆኑን
የጠቆመው መግለጫው፤ ለኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሊ ወንድማማች ህዝቦችና ለአገሪቷ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንደማይጠቅም አብራርቷል።

ይህን ጉዳይ በተመለከተ የሚመለከተው የመንግሥት አካል መርምሮ በቀጣይ ውሳኔ እንደሚሰጥበት መግለጫው አስታውቋል።

በማንኛውም ጊዜ፣ በየትኛውም ቦታ ችግር ቢፈጠር እንኳን በህግና በህግ አግባብ ብቻ መፍታት እየተቻለ በጅምላ በመፈረጅና ጥላቻን በመቀስቀስ ብጥብጥን
ለማነሳሳት መሞከር የሥርዓቱ ባህርይ አለመሆኑንም አትቷል።

በግጭቱ ሳቢያ ውድ ህይወታቸውን ባጡ ወገኖች እና በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥትና መላው ህዝብ ማዘናቸውን
መግለጫው አስታውሶ፤ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ብሎም ግጭቱን ለማስቆም እየተረባረቡ ባሉበት ወቅት የተላለፈው መረጃ ፈጽሞ ተቀባይነት
እንደሌለው አጽንኦት ሰጥቶታል።

መንግስት በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ወቅታዊ ግጭት ለማስቆም እና በሁለቱ ህዝቦች መካከል ለዘመናት
የኖረውን መልካም ግንኙነት ወደ ቀድሞው ለመመለስ  እየሰራ እንደሚገኝ መግለጫው አትቷል።


መግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ አጭር መግለጫየህዝብ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ግጭትን ማስቆም እንጅ ማባባስ የለበትም!

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ወቅታዊ ግጭት ለማስቆም እና በሁለቱ ህዝቦች መካከል ለዘመናት የኖረውን መልካም
ግንኙነት ወደቀድሞው ለመመለስ  መንግሥት እየሠራ ይገኛል።

በሁለቱ ክልሎች የተፈጠረው ግጭት እንዳይባባስ እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅትም ጥረቱ ከግብ ሊደርስ የሚችለው አፍራሽ የሆኑና ህዝብን ጥርጣሬ ላይ
የሚጥሉ መረጃዎች መሠራጨታቸው ሲቆም መሆኑን መንግሥት አምኖበት  በዚህ ጉዳይ ላይ አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወሳል። በዚሁ መሠረትም መገናኛ
ብዙሃንና ማህበራዊ ሚዲያዎች ከአፍራሽ ተግባር እንዲታቀቡ መንግሥት ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ መስጠቱ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣንም
ግጭቱን ተከትሎ የታዩ አፍራሽ አዝማሚያዎችን መሰረት በማድረግ ለሚመለከታቸው አካላት በላከው ደብዳቤ  ሚዲያዎች ከእንዲህ  ዓይነቱ ተግባር እንዲርቁ
አስጠንቅቋል። ከድርጊታቸው የማይታቀቡ አካላት ካሉም ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ ጥብቅ ማሳሰቢያ ተላልፏል። በተለይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ
ሚኒስትር በጉዳዩ ላይ መስከረም 6 ቀን 2010 መግለጫ በሰጡበት ወቅት በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ግጭት የሚያባብሱ የመገናኛ
ብዙኃን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ይህ የማይሆን ከሆነ መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈው እንደነበር
አይዘነጋም።

ይህ ሁሉ የሚደረገው ከኢትዮጵያ ህዝቦች መሠረታዊ ጥቅምና ፍላጎት በመነሳት እንደሆነ ዕሙን ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ  ህዝቦችም ሆኑ መንግሥት
የሚፈልጉት እናም በትክክልም  የሚበጃቸው ሰላም እንጅ ሁከት አይደለም። አንድነት እንጅ መከፋፈል አይደለም። ፍቅር እንጅ ጥላቻ፣ መተባበር እንጅ
መቃቃር፣ መተማመን እንጅ መጠራጠር፣ መከባበር እንጅ መናናቅ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ይህንን የህዝቦች መሠረታዊ ጥቅምና ፍላጎት በሚጻረር
መልኩ መረጃ ማሰራጨት የኢትዮጵያ ህዝቦችንና መንግሥትን ፍላጎት በመጻረር የሚፈጸም መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ  በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ድረ-ገፅ እና የቢሮ ሃላፊው ፌስቡክ ገጽ  ላይ  " የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል መንግስትና አገር
ሽማግሎች በኦሮሚያ ጥቃት ላይ የጋራ አቋም መግለጫ ይፋ አደረጉ" በሚል ርዕስ ማክሰኞ መስከረም 23 ቀን 2010 ዓ.ም. የተሰራጨው መረጃ
መንግሥት ያስቀመጠውን አቅጣጫ የሚቃረን፣ ከኢትዮጵያ ሶማሊ ሰላም ወዳድ ህዝብ እና መንግሥት እንዲሁም የፌዴራል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን
ከሚያራምድ ማንኛውም አመራር የማይጠበቅ፣ ለኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሊ ወንድማማች ህዝቦችና ለአገራችን ዘላቂ ሰላምና ልማት የማይጠቅም መሆኑ
ግልጽ ነው። በመሆኑም በተቀመጠው የመንግሥት አቅጣጫ መሠረት የሚመለከተው የመንግሥት አካል ጉዳዩን መርምሮ በቀጣይ ውሳኔ የሚሰጥበትም
ይሆናል።

የኮሙዩኒኬሽን እና የሚዲያ አካላት አሁንም ቢሆን ይህን መሰሉን መረጃ ከመልቀቅ እንዲሁም ይህን ለመሳሰሉ ዘገባዎች የአጸፋ ምላሽ ከመስጠት
እንዲታቀቡ አሁንም መንግሥት በድጋሚ በጽኑ ለማሳሰብ ይወዳል። የኮሙዩኒኬሽንና ሚዲያ ሥራዎቻችን ካለባቸው አገራዊ ተልዕኮ እንዲሁም ግጭቱን
አስመልክቶ መንግሥት በቅርቡ ከሰጠው አቅጣጫ አንጻር ለሁለቱ ህዝቦች ሰላምና አንድነት በሚጠቅሙ መረጃዎች ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ እና
ለተፈጠረው ችግር መቀረፍ የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ መንግሥት በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል።

የአገርን ሰላምና ጸጥታ የሚያደፈርስ ይህን መሰሉ መረጃ በምንም ዓይነት መልኩ የየትኛውንም ክልል መንግሥት፣ አመራር፣ የአገር ሽማግሌዎች ብሎም
የየክልሎቹን ህዝቦች ፍላጎት ይወክላል ብሎ መንግሥት በፍጹም አያምንም።

በማንኛውም ጊዜ፣ በየትኛውም ቦታ ችግር ቢፈጠር እንኳን በህግና በህግ አግባብ ብቻ መፍታት እየተቻለ በጅምላ በመፈረጅና ጥላቻን በመቀስቀስ ብጥብጥን
ለማነሳሳት መሞከር የምንከተለው ሥርዓት ባህርይ እንዳልሆነም ይታወቃል። በግጭቱ ሳቢያ ውድ ህይወታቸውን ባጡ ወገኖቻችን እና በ10 ሺህዎች
የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በተፈናቀሉበት ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥትና መላው ህዝብ እያዘኑና ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ብሎም ግጭቱን ለማስቆም
እየተረባረቡ ባሉበት ወቅት የተላለፈው መረጃ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው።

በኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 29 ስር ሀሳብን የመግለፅ እና የፕሬስ ነፃነት እና መብቶች የተረጋጡ ሲሆን እነዚህ መብቶች ያለገደብ የሚተገበሩ
አይደሉም። በህገ መንግስቱ በአንቀፅ 29/6/ ስር በዋናነት የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል  እንዲሁም የጦርነት
ቅስቀሳዎችን እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች በህግ ተከልክለዋል። ህጋዊ ገደቦችን ጥሶ መገኘትም በህግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ
በህገ መንግስቱ በአንቀፅ 29/7/ ስር ተጠቅሷል።

በማንኛውም ዓይነት ሚዲያ የሚቀርቡ መረጃዎች የሰው ልጆችን ስብዕና እና ነጻነት ወይም ስነምግባርን የሚጻረር ወይም የሌሎችን እምነት የሚያንኳስስ፤  
በመንግስት ጸጥታ ወይም በህገመንግስቱ መሰረት በተቋቋመ የመንግስት አስተዳደር ወይም በሀገር መከላከያ ሀይል ላይ የወንጀል ድርጊት የሚፈጽም፤  
የግለሰብን፣ የብሄር ብሄረሰብን፣ የህዝብን ወይም የድርጅትን ስም የሚያጠፋ ወይም በሀሰት የሚወነጅል፣ ብሔረሰብን ከብሄረሰብ የሚያጋጭ ወይም
በህዝቦች መካከል የእርስ በእርስ ግጭትን የሚያነሳሳ፤  ጦርነት የሚቀሰቅስ ይዘት ያላቸውን መረጃዎችን ማስተላለፍ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል በህግ
መደንገጉም ይታወቃል።

በመሆኑም እነዚህን መሠረታዊ የከሙዩኒኬሽንና የሚዲያ ህግጋት ድንጋጌዎችና መርሆዎች መተላለፍ የህግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል በመገንዘብ
ማንኛውም የኮሙዩኒኬሽንና የሚዲያ ሥራ ህግና ስነምግባርን የተከተለ እንዲሆን መንግሥት በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን በድጋሚ ያስተላልፋል።

የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሊ ወንድማማች ህዝቦች አንድነትና ትስስር በማይበጠስ ገመድ የተሳሰረ ነው። አሁን የሚታዩ ጊዜያዊ ግጭቶች የህዝቦቹን የጋራ
ጥቅምና ፍላጎት የማይወክሉ በመሆናቸው በራሳቸው በህዝቦቹ እና በመንግሥት የማያቋርጥ የጋራ ጥረት በአጭር ጊዜ ተፈትተው የቀደመው ሰላማዊ ግንኙነት
እንደሚመለስ የመንግሥት ጽኑ ዕምነት ነው።
admin@hebrezema.info
1