1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ መደበኛ ግንኙነታቸውን ለመጀመር ተስማሙ
July 8,2018
admin@hebrezema.info
1
አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 1 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ኤርትራ መደበኛ ግንኙነታቸውን ለመጀመር ተስማሙ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ
ተወያይተዋል።

በውይይታቸው ወቅትም የኤርትራ ኤምባሲ በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደግሞ በአስመራ እንዲከፈት
መስማማታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በዚህም ሁለቱ ሃገራት መደበኛ ግንኙነታቸውን ለመጀመር ተስማምተዋልም ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈም ሁለቱ ሃገራት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ለማደስ የሚያስችሉ ስምምነቶች መፈጸማቸውንም ነው የተናገሩት።

የየሃገራቱ አየር መንገዶች በረራ እንዲያደርጉና በወደቦች በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥
የሁለቱ ሃገራት ህዝቦች ተንቀሳቅሰው መስራት እንዲችሉ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች በጋራ አልምተው ተጠቃሚ ወደሚሆኑበት ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግረዋል ያሉት ጠቅላይ
ሚኒስትሩ፥ ሃገራቱ ሰላም ከፈጠሩ ቀጠናው የሰላምና የልማት ዞን ይሆናል ብለዋል።

ሰላም ጥቅም እንጅ ጉዳት እንደሌለው ጠቅሰው፥ ሰላም ለሁለቱም ሃገራት ህዝቦች ተጠቃሚነት ሚናው የጎላ መሀኑን
አስረድተዋል።

ለትውልድ ሰላምን በመስበክም በቀጣይነት የሁለቱን ሃገራት አንድነትና እኩል ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ
አውስተው፥ በስደት ያሉ ወገኖችም በክብር ወደ ሃገራቸው ይመለሳሉ ነው ያሉት።

አንድ ላይ በመሆንም በቀጠናው ያለውን እምቅ አቅም ተጠቅሞ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይቻላልም ብለዋል ጠቅላይ
ሚኒስትሩ በንግግራቸው።

ኤርትራውያን ላሳዩት ወደር የሌለው ፍቅር ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ከ20 ዓመት በፊት የተከሰተ ግጭትና ጥፋት ረስተን
በጋራ መበልጸግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ እየመከርን እንሰራለን ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች ለዚህ ቀን በመድረሳቸው እንኳን ደስ አላችሁ
በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ጥሪ ከልብ የመነጨና እውነተኛ መሆኑን በመግለጽ ለሰላም ጥሪውን የአወንታ ምላሻቸውን
ሰጥተዋል።

ሃገራቱ ባለፉት ጊዜያት ወደሰላም ለመምጣት ያደረጓቸውን ጥረቶች ጠቅሰው፥ አሁን ላይ ይህ ጥረት በመሳካቱ ጠቅላይ
ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ምስጋና ይገባቸዋል በማለት ምስጋናቸውን አድርሰዋል።

በሀለቱ ሃገራት መካከል ተቋርጦ የቆየው የመደበኛ ስልክ ግንኙነት መጀመሩም የሚታወስ ነው።