1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
በአምቦ ከተማ ከቀን ገቢ ግምት ጋር ተያያዞ ሐሙስ ሐምሌ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በተፈጠረ ግጭት ሳቢያ፣ ንብረትነታቸው የመንግሥት በሆኑ ሁለት
ተሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ፡፡

የኦሮሚያ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሐሙስ ዕለት በአምቦ ከተማ በተፈጠረው ግጭት
ንብረትነታቸው የዞኑ የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋምና የአምቦ ዩኒቨርሲቲ በሆኑ ተሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡  

የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋም ንብረት የሆነው ተሽከርካሪ ሙሉ በሙሉ በእሳት እንደነደደ የገለጹት አቶ አዲሱ፣ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ንብረት የሆነው
ተሽከርካሪ ደግሞ መስታወቱ በድንጋይ እንደተሰባበረ ገልጸዋል፡፡

ከቀን ገቢ ግምቱ ጋር በተያያዘ በክልሉ ግጭት ሊነሳ እንደሚችል መረጃው ቀደም ሲል ነበረ ያሉት አቶ አዲሱ፣ ይህንን የሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ የክልሉ
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እስከ ታች ድረስ ቅሬታ ሰሚ ቡድን አቋቁሞ ሲሠራ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

በ2009 ዓ.ም. በክልሉ አሥር ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የገለጹት አቶ አዲሱ፣ ከዚህ ውስጥ 45.7 በመቶ የሚሆነው ከመንግሥት ሠራተኞች፣
አሥራ ሰባት በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከንግድ ትርፍ የተሰበሰበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በክልሉ ውስጥ የንግድ ትርፍ አሰባሰብ ሥርዓቱ ችግር ያለበት
መሆኑን አስረድተው፣ የነጋዴው የቀን ገቢ ከዚህ በፊት በደንብ ያልተገመተ በመሆኑ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ታክስ እንደማይከፍሉ ጠቅሰዋል፡፡ ይህም
በመሆኑ ነጋዴዎች ወደ ሕጋዊ የታክስ ሥርዓቱ ሳይገቡ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም. በተካሄደው የቀን ገቢ ግምት ሥራ ከ46,000
በላይ ሕገወጥ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊ የታክስ ሥርዓት ማስገባት መቻሉን አብራርተዋል፡፡

በሕገወጥ መንገድ ሲነግዱ የነበሩ ነጋዴዎች ወደ ሕጋዊ የታክስ ሥርዓት በመግባታቸው ምክንያት ግጭቱ መከሰቱን አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡

ግጭቱ እኩለ ቀን አካባቢ የተቀሰቀሰ ቢሆንም ለሃያ ደቂቃ ብቻ የዘለቀና በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ አደጋ እንደሌለ አክለዋል፡፡

በአንድ አገር ዕድገት ለማምጣት ዜጎች ግብር የመክፈል ግዴታ እንዳለባቸው ጠቁመው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ብሎም በኦሮሚያ ክልል ግብር የመክፈል
ባህሉ ዝቅተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህ ዓመት በተሠራው የቀን ገቢ ግምትም ጉድለቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ ቅሬታ ያላቸው ትክክለኛ በሆነ መንገድ አሠራር ተዘርግቶላቸው
በክልሉ መንግሥት እየታየ ነው ብለዋል፡፡ ቅሬታቸውን ሰምቶና አገናዝቦ ትክክል ከሆነ ተቀብሎ፣ ትክክል ካልሆነ ደግሞ ትክክል ያልሆነበትን ምክንያት
በማስረዳት በአግባቡ እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህም ቢሆን ግን በተከናወነው ሥራ ከ46 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ነጋዴዎች ለምን ወደ ግብር መክፈል
ሥርዓት መጣን በሚል ስሜት ተነሳስተው ወዳልሆነ አቅጣጫ በመሄድ የፈጠሩት ግጭት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

‹‹በአምቦ ከተማ ብቻ ሳይሆን በመላው ኦሮሚያ ግጭት ለማነሳሳት ሴራ እየተሸረበ እንደነበር እናውቃለን፤›› ያሉት አቶ አዲሱ፣ ‹‹ታስቦ የነበረው
በክልሉ ሕዝብና ንብረት ላይ ከዚህ የከፋ ጉዳት በማድረስ ኦሮሚያን እንደከዚህ ቀደሙ የሁከትና የረብሻ መናኸሪያ ማድረግ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በመላው ኦሮሚያ ተመሳሳይ አመፅና ረብሻ ተፈጥሮ ክልሉ ባለፈው ዓመት ወደነበረበት የፀጥታ ችግር እንዲመለስ የታቀደ ቢሆንም ጉዳዩ ገና ከጅምሩ
ነው የተቀጨው፤›› ብለዋል፡፡

የረብሻው ዓላማ መንገድ በመዝጋት በአምቦ ከተማ ላይ ሰፊ ጉዳት እንዲደርስ እንደነበር የጠቆሙት አቶ አዲሱ፣ በክልሉ ሕዝብና በፀጥታው አካላት
አማካይነት ገና ከጅምሩ አጥፊዎችን በመያዝ የከፋ ጉዳት አለመድረሱን ገልጸዋል፡፡
admin@hebrezema.info
1