1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
admin@hebrezema.info
1
ጠንካራ የፍትህ ሥርዓት ይገንባ!
May 11, 2017
ጠንካራ የፍትህ ሥርዓት ለአንድ አገር ዘላቂ ሰላምና ፈጣን እድገት ወሳኝ ነው። በኢትዮጵያም ለፍትሐዊ፣ ተደራሽና
ቀልጣፋ የፍትህ ሥርዓት መዘርጋት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ «የሕግ የበላይነት
ለዘላቂ ሰላምና ለሕዝቦች አንድነት» በሚል መሪ መልዕክት ከሚያዝያ 30 እስከ ግንቦት 6 ቀን 2009 ዓ.ም የሚካሄደው
የፍትህ ሳምንትም ከተግባራቱ አንዱ ነው።

በአለፉት ዓመታት የተከበሩት የፍትህ ሳምንታት የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችንና ባለድርሻ አካላትን በአንድ መድረክ
በማገናኘት በርካታ ግብአቶች የተገኘባቸው ነበሩ። እነዚህም መድረኮች ኅብረተሰቡ በፍትህ አሰጣጥ ዙሪያ ያሉትን ችግሮች
በግልጽ እንዲያቀርብ ዕድል በመፍጠር የለውጥ ተሳታፊነቱንና ባለቤትነቱን እንዲያረጋግጥ አስችለዋል። የፍትህ አካላት
አሠራራቸውን ፈትሸው ክፍተቶቻቸውን በማሻሻል ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እንዲያስመዘግቡ እገዛ አድርገዋል።

የዘንድሮውም የፍትህ ሳምንት የተገኙትን ትሩፋቶች ከማጠናከር ባሻገር ኅብረተሰቡ የለውጥ ንቅናቄውን በማጠናከር
በተለይ ጥልቅ ተሃድሶው በተጀመረበት ግለት እንዲቀጥል በማድረግ በፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ የሚታዩትን የመልካም
አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ጉልበት ይሰጣል ተብሎ ይታመናል። ይሁንና በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች ከስር መሠረቱ
ለመፍታት የሚያግዝ እንዲሆን ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣት አጀንዳ ማድረግ ይገባል።

የዘንድሮው የፍትህ ሳምንት ሲከበር በዘርፉ ዋና ተዋናይ በሆኑት ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊስ እንዲሁም ማረሚያ ቤቶች ዘንድ
የሚታየው ቅንጅት የጎደለው ተግባር አንዱ አጀንዳና ሊፈታ የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት መሆን
አለበት። የቅንጅት ሥራ በተገቢው መንገድ አለመከናወኑ ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዳያገኙ በማድረግ ምሬት ውስጥ
ከሚከቱ ጉዳዮች አንዱ ነው። በመሆኑም ተቋማቱ የሚነሳባቸውን ቅሬታ በዘለቄታው ለመፍታት መትጋት አለባቸው።

በሌሎች አገራት የሚሰራባቸውን ሥርዓቱን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ተሞክሮዎችን በመቅሰም የቅሬታ ምንጮችን ለአንዴና
ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ይገባል። በፍትህ ሥርዓቱ በተለያየ ዘርፍ የሚገኙ ባለሙያዎችም እርስ በእርስ ከመጠላለፍና
ከመናናቅ ወጥተው ትክክለኛ ፍትህ በማስፈን የወጡበትን ኅብረተሰብ በቅንነት ለማገልገል ቁርጠኛ ይሆኑ ዘንድም ሳምንቱ
ሲዘከር ሊታሰብበት ይገባል።

በፍትህ ዘርፉ ዜጎችን ለምሬት የሚዳርገው የእጅ መንሻ ጉዳይ ሊታሰብበት የሚገባው ሌላው አጀንዳ ነው። በእጅ መንሻ
ንጹሃን ያለጥፋታቸው የሚፈረድባቸው ፣ወንጀለኞች ደግሞ ለጊዜውም ቢሆን የፍስሐ ቀናቸውን የሚያጣጥሙበት ዘመን
ይበቃል ሊባል ይገባል። መንግሥት ለእዚህ የሚረዱ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ሲሆን፤ አለመጠናከሩና ተጨበጭ
ለውጥ ያለማምጣቱ ጉዳይ ቀሪ የቤት ሥራ እንዳለ አመላካች ነው።

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች በእጅ መንሻ ለጊዜያዊ ጥቅም እንዳይደለሉ መንግሥት ኢኮኖሚያዊ ድጋፎችን ለማመቻቸት
የሚያደርገው ተግባር ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም፤ እነርሱም በዜጎች ንጹህ ላብ የሚገኘው ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ይቅርብን
የሚል ህሊናዊና ሞራላዊ ተጠያቂነትን ሊላበሱ ይገባል። በዋነኝነት ግን ከታች ጀምሮ ለህሊናዊ ተጠያቂነት ዘብ የሚቆም
ዜጋ ለማፍራት በትምህርት ቤቶች በሚሰጡ የዜግነትና የሥነ ምግባር ትምህርቶች ዜጎችን ለመቅረጽ የሚደረገው ጥረት
መጠናከር አለበት። ንድፈ ሀሳቡ በተግባር የሚተረጎምበት መንገድም ሊታስበበት የሚገባ ጉዳይ በመሆኑ አጽንኦት ይሻል።
የፍትህ ሥርዓቱ ስኬት ቀኝ እጅ ኅብረተሰቡ ነው። ወንጀል እንዳይፈጸም ከመከላከል ጀምሮ የተዛባ ፍትህን የሚታገል
ትውልድ በመቅረጽ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። የወንጀል ድርጊቶችን በማጋለጥ እንዲሁም ተፈጽሞ ሲገኝ ሀቅን
መሠረት ያደረገ ህሊናዊ ምስክርነት በመስጠት ጥፋተኛ ተገቢውን ውሳኔ እንዲያገኝ የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል።

ኅብረተሰቡ በፍትህ አሰጣጡ ቁልፍ ተሳታፊ በመሆኑ የተሰጠውን ከፍ ያለ ሚና የሚመጥን ተግባር ይጠበቅበታል። ሕግ
አቅም ላጣ ምርኩዝ መሆኑን በማሰብ በእኔነት ስሜት ለሃቅ መቆም እና ተሳትፎውን ማጠናከር አለበት።

በፍትህ ሥርዓቱ በእጥረትነት የሚነሳውን የተደራሽነት ጉዳይ ለመፍታት የተተገበሩት ተዘዋዋሪ እና የክላስተር ችሎቶች
መጠናከት አለባቸው፤ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት የተጀመረውም ጥረት እንዲሁ። ብቁና በቂ የሰው ኃይል
የማፍራቱም ጉዳይ ጊዜ ሳይሰጠው ሊፈታ ይገባል። የፍትህ ሳምንት ሲዘከር ከበአልነት ስሜት ባሻገር የተጠቀሱትን
ጉድለቶች በመፍታት ቁርጠኝነትና የዜጎችን እርካታ በማረጋገጥ መንፈስ እንዲሆን እንመኛለን።