ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቤኒን አቻቸው ጋር ተወያዩ

October 22, 2021

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቤኒን አቻቸው ኦሬሊየን አግቤኒቺ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ።


39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል። ከስብሰባው በተጓዳኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቤኒን አቻቸው ኦሬሊየን አግቤኒቺ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።


የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹን ውይይት የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ኢትዮጵያ እና ቤኒን የሁለትዮሽ ትብብራቸውን በሚያጠናክሩባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል።


ቤኒን በአዲስ አበባ ኢምባሲዋን ለመክፈት መዘጋጀቷንና አምባሰደር መሾሙንም በውይይቱ ላይ ተነስቷል ብለዋል። ቤኒን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር እንደምትሻና በሁሉም መስኮች ለመተባበር ዝግጁ መሆኗንም አግቤኒቺ አረጋግጠዋል።


ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሌሎች የአፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።