1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
ኮንትሮባንድ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተከለከሉ ነገሮችን ይዞ መገኘት ወይም መግዛት ህገወጥ ተግባር መሆኑን ለማመላከት እኤአ ከ1529 ጀምሮ
ጥቅም ላይ መዋሉ ይነገራል።

የቃሉ ህጋዊ ትርጉም የአንድን ሀገር ህግ በሚቃረን መልኩ እቃዎችን ከማስወጣትና ማስገባት እንዲሁም የተከለከሉ ነገሮችን ከማምረትና ባለቤት ከመሆን
ጋር ይያያዛል።

በኢትዮጵያ የኮንትሮባንድ ንግድ መቼና እንዴት እንደተጀመረ የሚገልጽ የተሟላ ማስረጃ ባይኖርም እንቅስቃሴው ከተጀመረ ግን በርካታ ዓመታትን
አስቆጥሯል።

የኢትዮጵያ ጉሙሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የጉሙሩክ ህጎችን በመተላለፍ የተከለከሉ፣ ገደብ የተደረገባቸው ወይም
የንግድ መጠን ያላቸውና የጉሙሩክ ሥነ ስርዓት ያልተፈጸመባቸው ዕቃዎችን በድብቅ ወይም ከህጋዊ መተላለፊያ መስመሩ ውጪ ወደ አገር ማስገባት፣
ከሀገር ማስወጣት ወይም መሞከር ወይም ደግሞ በህጋዊ መንገድ የወጡ እቃዎችን ህጋዊ ባልሆነ መንገድ መልሶ ማስገባት የኮንትሮባንድ ወንጀል መሆኑን
ይደነግጋል። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የኮንትሮባንድ እቃዎችን ማጓጓዝ፣ ማከማቸት፣ መያዝ፣ ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መግዛትም እንዲሁ።

ሀገሪቱ ኮንትሮባንድን ለመግታት የተለያዩ ህጎችንና መመሪያዎችን ተግባራዊ ታድርግ እንጂ  አሁንም ድረስ እቃዎችን በህገ ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ
የማስወጣትና ማስገባት እንቅስቃሴው የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገቷ ሳንካ እንደሆነ ነው።

የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውን የመቆጣጠር ሃላፊነቱ የተሰጣቸው የፌደራል ፖሊስና ሌሎች ህግ አስከባሪዎች በየቀኑ በርካታ እቃዎች ከሀገሪቱ ሲወጡና
ሲገቡ በቁጥጥር ስር ያውላሉ። ይህ ማለት ግን ከጸጥታ አካላቱ አይንና ጆሮ ተሰውረው ወደ ሀገሪቱ የሚገቡና የሚወጡ እቃዎች የሉም ማለት እንዳልሆነ
ከግንዛቤ ውስጥ መግባት ይኖርበታል።

በየቀኑ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገሪቱ ሊገቡ ሲሉ ከሚያዙ እቃዎች መካከል የኤሌክትሮኒክስና የኤሌክትሪክ እቃዎች፣ ልዩ ልዩ አልባሳት፣ ሽቶዎች፣
መዋቢያዎች፣ ወሲብ ቀስቃሽ ፊልሞች፣ ደህንነታቸውና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ መድሃኒቶች፣ አደንዛዥ እጾችና ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ የጦር
መሳሪያዎችና የመሳሰሉት ይገኙበታል። እነዚህ እቃዎች በሱዳን፣ ኤርትራ፣ ኬንያና ጂቡቲ በኩል ወደ ሀገሪቱ እንደሚገቡም ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።

የሀገሪቱ አረንጓዴ ወርቅ በመባል የሚታወቀውን ቡና ጨምሮ ልዩ ልዩ የቁም እንስሳት፣ የእንስሳት ቆዳ፣ አልባሳት፣ ሲጋራ፣ ትምባሆ፣ ማዕድን፣ ጥራጥሬ፣
ጫት፣ ጤፍ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ስኳር፣ ዘይት፣ ነዳጅና መሰል እቃዎች ደግሞ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት ሀገራት ይወጣሉ።

ለኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ለመንግስት የሚከፈልን ታክስ ሽሽትና በህገ ወጥ ውድድር ተጠቃሚ ለመሆን መሻት
ቀዳሚው ምክንያት ነው። እቃዎቹና ሰነዶቻቸው የሀገሪቱን ህግና መመሪያ መሰረት ያደረጉ መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ የተቋቋሙ የጉሙሩክ
መቆጣጠሪያ ጣቢያዎችን ሽሽትም ሌላኛው ምክንያት ነው።

የሀገሪቱን ልማት፣ ሰላምና ጸጥታ የማይፈልጉ አካላትም የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስና ልዩ ልዩ ወንጀሎችን ለመፈጸም እንዲያመቻቸው
የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችንና ፈንጂዎችን ያስገባሉ። ከስራ አጥነት ጋር የተያያዙ ምክንያቶችም እንዲሁ በዘርፉ የሚሳተፉ ሰዎች ቁጥር ለመጨመሩ
በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

በኮንትሮባንድ መልኩ የሚገቡ እቃዎች ምንም አይነት ታክስና ቀረጥ ስለ ማይከፈልባቸው በህጋዊ መንገድ ከሚገቡት ጋር ሲነጻጸሩ ዋጋቸው ዝቅተኛ ነው፡፡
ይህ ደግሞ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ምርጫ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ጥቁር ገበያው በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ትርፍ ይገኝበታል፡፡ ይህም
የሀገሪቱን ህግና ስርዓት አክብሮ በሚንቀሳቀሰው ነጋዴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡

የሶማሊያ አለመረጋጋትና የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲሁም የኢኮኖሚ ድቀቷ በኢትዮጵያ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ ማበርከቱን
ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውን ለመግታት የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር እየጠነከረ በሄደ ቁጥር ህገ ወጥ ንግዱ የሚከናወንበት መንገድም በዚያው ልክ
እየረቀቀ መጥቷል። ክትትልና ቁጥጥር የማይደረግባቸውን አካባቢዎች በማጥናት እቃዎቹን በእግርና በጋማ ከብቶች ድንበር ማሻገርን ጨምሮ ህገ ወጥ
አዘዋዋሪዎቹ የኮንትሮባንድ እቃዎችን በተሽከርካሪ ጎማዎች፣ በሮች፣  የነዳጅ ታንከሮችና በሌሎች የተሽከርካሪ ምስጢራዊ ቦታዎች ውስጥ ሰውረው
ያስወጣሉ፤ ያስገባሉ።

የኮንትሮባንድ እቃዎች ከሌሎች ህግና ስርዓት ካሟሉ እቃዎች ጋር ተቀላቅለው የሚወጡበትና የሚገቡበት መንገድ መኖሩንም በጉዳዩ ላይ የተደረጉ
ጥናቶች ይጠቁማሉ። ህገ ወጥ ነጋዴዎቹ ስነ ምግባር ከጎደላቸው ጥቂት የጉሙሩክ ባለሙያዎች ጋር በመደራደር እቃዎችን ከህግ አግባብ ውጭ ከሀገር
እንደሚያስወጡና እንደሚያስገቡም ይታወቃል።

በዚህ መሰሉ ስራ የተሰማሩ አካላት የኮንትሮባንድ እቃዎችን የሚያስወጡበትና የሚያስገቡበት አንደኛው በር ሲዘጋባቸው ሌላ ምስጢራዊ ቦታ በማፈላለግ
የክትትልና ቁጥጥር ስራውን አስቸጋሪ ከማድረጋቸውም ባሻገር እንደ ጊኒርና ነገሌ በመሳሰሉ መሸጋገሪያዎች ደግሞ አዘዋዋሪዎቹ ህገወጥ የጦር
መሳሪያዎችን ታጥቀው እስከ መንቀሳቀስ ይደርሳሉ። ህገ-ወጦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚደረገው ጥረትም የኢትዮጵያ ጸጥታ ሃይሎች ምትክ አልባ
ህይወታቸውን ጭምር ከፍለዋል።

ድሬዳዋ፣ ጂግጂጋ፣ ሀረር፣ ገዳማይቱና አዳማ የኮንትሮባንድ ንግድ የሚካሄድባቸውና የማከማቻ ማእከላት መሆናቸው በጥናት ተለይቷል። መዲናችን አዲስ
አበባ ደግሞ በህጋዊና ህገወጥ መንገድ የገቡ እቃዎች እኩል ይቸበቸቡባታል። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች
በየመንገዱ ጠርዝ በተለይ በምሽት የኮንትሮባንድ እቃዎች ሲቸበቸቡ ማየት ተለምዷል።

በአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት በሚደረገው ቁጥጥርና ክትትል በኮንትሮባንድ መልኩ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡና የሚወጡ እቃዎች አመታዊ አማካኝ የዋጋ ግምት
ግማሽ ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ከገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ 337
ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ገቢና ወጪ እቃዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

በሞያሌ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የነገሌ ቦረና መቆጣጠሪያ ጣቢያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 27 ሚሊዮን ብር ግምት
ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎችን ይዟል፡፡

ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ደግሞ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በህገ ወጥ
መንገድ ሲዘዋወሩ ከተያዙ ንብረቶች ከ105 ሚሊዮን በላይ ብር ለመንግሥት ገቢ ሆኗል፡፡

በባለስልጣኑ የጎንደር ጉሙሩክ መቅረጫም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚበልጥ የኮንትሮባንድ እቃ መያዙንና እቃዎቹን
ሲያጓጉዙ የተገኙ 32 ተሽከርካሪዎችና 103 ግለሰቦች ተይዘው ጉዳያቸው ለህግ መቅረቡን ይፋ አድርጓል፡፡

የቅርብ ጊዜ መረጃዎችን ብንመለከት እንኳን በሰኔ ወር የመጀመሪያ ሳምንት የጅማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ምንም አይነት የመንግስት ታክስና ቀረጥ
ያልተከፈለበቸው ከ1 ሚሊዮን በላይ ግምት ያላቸው የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ ምግብ ነክ ቁሳቁሶች፣ አልባሳትና ጫማዎች፣ መዋቢያዎች፣ የተሽከርካሪ
መለዋወጫዎች፣ ቡናና መሰል እቃዎች በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ ይዟል።

በተመሳሳይ የጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትም ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ 64 የቀንድ ከብቶችን፣ 120 ፍየሎችና 190 በጎችን ጨምሮ
ሌሎች እቃዎች በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡና ሊገቡ ሲሉ በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

የተለያዩ መኪናዎችና ሞተር ሳይክሎችን ጨምሮ ኤሌክትሮኒክስ፣ አልባሳትና ምግብ ነክ ሸቀጣ ሸቀጦች እንዲሁም ዝንጅብል በያቤሎና ቡሌሆራ
መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ተይዘዋል።

ለአብነት የቅርብ ጊዜ መረጃዎችን አነሳን እንጂ መሰል የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያደረሱ መሆናቸው
አይታበልም።

ኮንትሮባንድና ከንግድ ማጭበርበር ጋር የተያያዙ ወንጀሎች በህጋዊው የንግድ እንቅስቃሴ፣ በህዝብ ደህንነት፣ በመንግስት ገቢና በሌሎች የሀገሪቱ
ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የሚያደርሱትን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ይቻል ዘንድ መንግስት የጉሙሩክ አዋጁን ከማሻሻል በተጨማሪ
የተጠናከረ የቁጥጥርና ክትትል ስርዓት ዘርግቷል።

የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውን ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ለመግታት ያመች ዘንድም የኮንትሮባንድ እቃዎችን የሚይዝና የሚጠቁም ማንኛውም ሰው
ከግኝቱ 20 በመቶውን የሚያገኝበት መመሪያ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ መመሪያውን አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ካለማወቁም በተጨማሪ
በመመሪያው ጥቂቶች አለአግባብ ኪሳቸውን ሲያደልቡበት መቆየተቻውን የባለሥልጣኑ የህግ ማስከበር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘመዴ ተፈራ
ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ኮንትሮባንድ መንግሥት ወደ ሀገር ከሚገቡና ከሚወጡ እቃዎች ማግኘት የነበረበትን ገቢ በማሳጣት የሀገሪቱን የልማት ፕሮግራም ሊያጓትተው ይችላል፡፡
በህግ አግባብ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችን ከውድድር ውጭ በማድረግ የስራ አጥነት ቁጥሩን ይጨምራል፡፡ በኮንትሮባንድ መልኩ የሚገቡ ወሲብነክ ፊልሞችና
አደንዛዥ እጾች የዜጎችን መልካም ስነ ምግባርና ማህበራዊ ግንኙነት ያቃውሳሉ፡፡  

በህገወጥ መንገድ የሚገቡ የጦር መሳሪያዎችም የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት በማናጋት ልማቱንና ዴሞከራሲያዊ ስርዓቱን ወደ ኋላ ሊመልሱት ይችላሉ፡፡
ታሪካዊ ቅርሶቻችንንም ሳይቀር ልናጣ የምንችልበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖም እንዲሁ  በቀላሉ
የሚታይ አይደለም፡፡

ኮንትሮባንድ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገት ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ከተቀመጡ አማራጮች መካከል በዚህ መሰሉ
ድርጊት የሚሳተፉ አካላትን በህግ እንዲቀጡ ማድረግ አንዱ ነው፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ በርካታ ጉዳዮች ይቀርቡለታል፡፡ ለበርካቶችም የሚቀርቡ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አግባብ ካላቸው
የሀገሪቱ ህግጋት ጋር በማገናዘብ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ በቅርቡ ውሳኔ ከሰጠባቸው መዛግብት መካከል አንዱን
ለማሳረጊያነት እንመልከት፡፡

በሽር አህመድ መጋቢት 17 ቀን 2008 ዓ.ም 600 ጣሳ ሺሻና 112 ሺህ 752 ፓኬት ትሪደንት ማስቲካ ከደብረ ብርሃን ወደ አዲስ አበባ ሲያጓጉዝ
ተይዞ በጉሙሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 168(2) መሰረት የኮንትሮባንድ ወንጀል ክስ ተመሰርተበት፡፡

አግባብ ካለው የመንግሥት መስሪያ ቤት ማስቲካውን ለህብረተሰቡ ለማቅረብ የሚያስችል ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖረው ሲያጓጉዝ በመገኘቱ ደግሞ በምግብ፣
መድሃኒትና ጤና እንክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 661/2002 አንቀጽ 53(1)(ሸ) መሰረት ሌላ ክስ ቀረበበት፡፡

ሁለቱንም ጉዳዮች የተመለከተው የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቀረቡለትን ማስረጃዎች መርምሮ በ12/10/2009 በዋለው ችሎት
ግለሰቡ ላይ የአምስት ዓመት ጽኑ እስራትና የ50 ሺ ብር መቀጮ ወስኖበታል፡፡

ይሁን እንጅ ግለሰቡ በውሳኔው ቅር በመሰኘቱ ጉዳዩን በይግባኝ ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ወስዶታል፡፡ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱም በስር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ
የህግ ጥሰት አለ የለም? የሚለውን መርምሮ የእስራት ቅጣቱ ወደ ሶስት ዓመት ከሶስት ወር የገንዘብ መቀጮው ደግሞ ወደ ብር 20 ሺህ ዝቅ እንዲል
አድጓል፡፡

በዚህ መሰሉ ህገ ወጥ ንግድ የህዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ መንግሥት ከዘርፉ ማግኘት ያለበትን ገቢ የሚያሳጡ፣ ህግና ስርዓት አክብሮ
የሚንቀሳቀሰውን ነጋዴ ከገበያ ውጭ የሚያደርጉ፣ የሀገሪቱን ሰላምና ደሀንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እቃዎችን በሚያዘዋውሩ ሰዎች ላይ ከጥፋታቸው
የሚያርም ሌላውንም የሚያስተምር ቅጣት ማስተላለፉ ብቻውን የታሰበውን ለውጥ ያመጣል ተብሎ አይታሰብም፡፡

ከህብረተሰቡ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ መስራት ከምንም በላይ ደግሞ የኮንትሮባንድን መዘዞች ህብረተሰቡ እንዲያውቃቸው ማድረግ እንቅስቃሴውን
ለመግታት ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ የህብረተሰቡ የግንዛቤ አድማስ እየሰፋ በሄደ ቁጥር ደግሞ ህገ ወጦችን አሳልፎ ከመስጠት ወደ ኋላ አይልም፡፡
በሂደትም ለመንግሥት የሚገባውን ላለመክፈል የድብብቆሽ ጨዋታ መጫወቱ ቀርቶ “የቄሳርን ለቄሳር” የሚል ማህበረሰብን መገንባት ይቻላል፡፡
admin@hebrezema.info
1