የድሬዳዋ ልዩ ኃይል የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ዘመቻ ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ሊያቀና ነው

July 16,2021

የሀገርን ህልውና ለመጠበቅና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ዘመቻ ለመሳተፍ የተዘጋጁ የድሬዳዋ ልዩ ኃይል ወደ ስፍራው ለማቅናት አሸኛኘት ሊደረግለት መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።


የኮሚሽኑ የለውጥ ሥራዎችና የሕዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ዳይክሬቶሬት ተወካይ ረዳት ኢንስፔክተር ባንተአለም ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኮሚሽኑ አመራሮችና የፖሊስ አባላት የሀገርን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ በሚደረግ እንቅስቃሴ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው ። የሀገርን ታላቅነትና ዕድገት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ፈርጀ ብዙ ተግባራት በምንም በማንም እንዳይስተጓጐሉም መስዋትነት ይከፈላሉም ብለዋል።


ይህን ዕውን ለማድረግ የኮሚሽኑ ልዩ ኃይል አባላት ሽብርተኛውን የህወሓት ጁንታ ቡድን ለሕግ ለማቅረብና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተላለፈውን ጥሪ ተከትሎ ወደ ስፍራው ማምሻውን እንደሚሸኙ አስታውቀዋል።


ረዳት ኢንሰፔክተር ባንተ ዓለም ፤ ሽብርተኛው ቡድን ያነገበው ሀገር የማፈራረስ ተልዕኮ በተባበረ ክንድ ይከሽፋል፤ ሀገራችንም ትሻገራለች ብለዋል። የድሬዳዋ ፖሊስ ታላቋን ኢትዮጵያ ለመገንባት እያከናወኑ ያሉ ተስፋ ሰጪ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አመልክተዋል። ወደ ሕግ ማስከበር ተልዕኮ ስፍራ የሚሸኘው የልዩ ኃይል አሸኛኘት ሥነ ሥርዓት ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድን ጨምሮ የካቢኔ አባላት፣የሀገር ሽማግሌዎችና የህብረተሰብ ተወካዮች እንደሚገኙ ይጠበቃል።