1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
admin@hebrezema.info
የኢህአዴግ ጉባኤ አሠራር ይስተካከል ታዋቂ ሰዎች ተናግረዋል
January 11, 2017
በ2007 ዓ.ም መጨረሻ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዷን አጠናቃ ወደ ሁለተኛው የእቅድ ዘመን
የተሻገረችው ሠፋፊ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ግብ በመጣል ነው። ይሄንኑ ግብ ከዳር ለማድረስም በዕቅድ ዘመኑ ዋዜማ ላይ በፌዴራል
መንግሥት አማካኝነት በተለያዩ ዘርፎች ግንባታዎችን ለማከናወን በርካታ የመሠረት ድንጋዮች ተቀምጠዋል። ከአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር
በፊት ከተጣሉት የመሠረት ድንጋዮች የተወሰኑት ግንባታቸው የተጀመረ ሲሆን፤ የተቀሩት ፕሮጀክቶች አሁንም ድረስ ከመሠረት ድንጋይ
አልዘለሉም።

በእቅድ ዘመኑ በትምህርት ዘርፍ 11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን በመገንባት በ2012 ዓ.ም 77 ሺህ ተማሪዎችን ተቀብለው
እንደሚያስተናግዱ ግብ ተጥሏል። የትምህርት ሚኒስቴር የኮምንኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ ጣፋ፤ የ10ሩ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ
መጀመሩንና በአማካይ 20 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል፡፡ የኦዳ ቡልቱ ዩኒቨርሲቲ ሥራ ግን ከካሳ አለመከፈል ጋር ተያይዞ ግንባታው
እስከአሁን አለመጀመሩን አስታውቀዋል።

በጤናው ዘርፍም በአዲስ አበባ በአንድ ቢሊዮን ብር አንድ የካንሰርና የልብ ማዕከል ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ከተጣለ ከአንድ
ዓመት በላይ ተቆጥሯል፡፡ በቅርቡ ግን የዲዛይኑ ሥራ ተጠናቆ ወደ ግንባታ መገባቱን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጤና መሠረተ ልማት
ዳይሬክተር ኢንጅነር ታደሰ የማነ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በኮልፌ፣ አቃቂ ቃሊትና ቦሌ ክፍለ ከተሞች ሦስት ቢሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቁና
አንደ ሺ 500 አልጋ ያላቸው ሆስፒታሎች ግንባታን ለማከናወን በ2007 የመሠረት ድንጋይ ቢጣልም እስከአሁን ሥራቸው አልተ
ጀመረም።
በትራንስፖርት ዘርፉም በአየር፣ በባቡርና በመንገድ መሠረተ ለማት ሰፋፊ ግቦች ተቀምጠዋል። በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ በዕቅድ ዘመኑ
መጨረሻ አምስት በጠጠርና አምስት በአስፓልት ደረጃ ኤርፖርቶችን ለመገንባት እቅድ ተይዟል። ከእነዚህ ኤርፖርቶች መካከልም
በ2007 ዓ.ም መጠናቀቂያ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የመሠረት ድንጋዩ የተቀመጠው የነቀምት ኤርፖርት አንዱ
ነው።

የኢትዮጵያ ኤሪፖርቶች ድርጅት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድም ተክሉ የነቀምት ኤርፖርት በመከላከያ
ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ግንባታውና ዲዛይኑ ጎን ለጎን ከአንድ ወር በፊት መጀመሩን ተናግረዋል። ከካሳ ጋርም እየተሠራ ያለ ሥራ
እንዳለ ገልጸዋል። «ግንባታና ዲዛይንን ጎን ለጎን ማካሄድ በመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ ከእጥፍ በላይ የጊዜና የገንዘብ ወጪ አድርሰዋል።
በዚህ ፕሮጀክት እንደዚያ ዓይነት ችግር ላለመደገሙ ዋስትናው ምንድን ነው?» ተብለው የተጠየቁት አቶ ወንድሙ፤ በምላሻቸው
«ኢንተርፕራይዙን የሚቆጣጠር አማካሪ ስላለ ችግሩ አይከሰትም» ብለዋል።

በመንገድ ዘርፍም በመጀመሪያው የዕቅድ ዘመን የተደረሰበትን 110 ሺህ ኪሎ ሜትር በእጥፍ ለማሳደግ ግብ ተጥሏል። የኢትዮጵያ
መንገዶች ባለሥልጣን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬከተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ እስከአሁን ግንባታቸው ያልጀመሩትን
የመንገድ ፕሮጅክቶችን በተመለከተ መረጃ ለመስጠት ተደጋጋሚ ቀጠሮ ከመስጠት በዘለለ ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡

በባቡር መሠረተ ልማት በአንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ታቅደው ወደ ሁለተኛው የእቅድ ዘመን ከተላለፉት ውስጥ
የአምቦ፣ ጅማና በደሌ የባቡር መስመሮች የመሠረት ድንጋያቸው በ2007 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተቀምጧል፡፡
ግንባታቸው ግን እስከአሁን አልተጀመረም። የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ፤ «ግንባታው
የዘገየው በአቅም ውስንነት ነው» ብለዋል።

ሌላው በ2007 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ኃለማርያም ደሳለኝ አማካኝነት የመሠረት ድንጋዩ የተቀመጠውና አንድ ነጥብ አምስት
ቢሊዮን ብር የሚፈጀውና ከ50ሺ በላይ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለው የድሬዳዋ ዘመናዊ ስታዲየም ግንባታም እስከአሁን ሥራው
አልተጀመረም። የከተማ አስተዳደሩ የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ አቶ የኑስ ሰርዴም፤ ግንባታው በቀጣይ ዓመት እንደሚጀመር ነው
ያስታወቁት፡፡

በዕቅድ ዘመኑ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለላቻው የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከልም የመቀሌው 30 በመቶ፣ የኮምቦልቻ 20 በመቶ፣
የአዳማ አምስት በመቶ እና የድሬዳዋው ሁለት በመቶ ሥራቸው ተጠናቋል። ነገረ ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የመሠረት
ድንጋዩ የተጣለው የጅማው የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታን እስከአሁን አልተጀመረም። በሚኒስትር ድኤታ ማዕረግ የኢንዱስትሪ ፓርኮች
ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ሲሳይ ገመቹ በቀጣይ ሳምንት ወደ ግንባታ ለመሸጋገር ስምምነት እንደሚፈጸም
ተናግረዋል።
ከመሠረት ድንጋይ ያልዘለሉት ፕሮጀክቶች ምክንያትንና የተቀመጠውን የመፍትሔ አቅጣጫ በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡን ጥያቄ
ያቀረብንላቸው የመንግሥት ኮምንኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ድኤታ አቶ ዛዲግ አብርሃ፤ መረጃውን መስጠት ያለባቸው
የእያንዳንዱ ተቋማት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች መሆናቸውን ገልጸው፤ «መረጃዎቹን አንሰጥም ካሉ ግን ልናግዛችሁ እንችላለን» ብለዋል።

ከፋይናንስ ችግር ጋር ተያይዞ ምላሽ እንዲሰጡን ጥያቄ ያቀረብንላቸው በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና
ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ፤ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ መቼ ይጀመራሉ፣ መቼ ያለቃል፣ ስንት ብር ይፈለጋል፣ የሚሠራው
ማነው፣ የሚለውን የሚለዩት አስፈፃሚ ተቋማት ናቸው። ሚኒስቴሩ የሚያገባው ጉዳይ የለም ብለውናል።

በትራንስፖርት ዘርፍ (በመንገድ፣ ባቡርና ኤርፖርት) ግንባታቸው ያልተጀመሩ ፕሮጀክቶችን አስመልክተው የትራንስፖርት ሚኒስቴር
የኮምንኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ በሰጡት ምላሽ፤ በዘርፉ የተያዙት እቅዶች ከፍተኛ ገንዝብ የሚጠይቁ በመሆናቸውና
ገንዘቡ ስላልተገኘ ግንባታው ሊዘገይ ችሏል ነው ያሉት፡፡ ሁሉንም ግንባታዎች በዕቅድ ዘመኑ እንዲጠናቀቁ ሁሉም ባለድርሻ አካላት
በባለቤትነት መረባረብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

አጎናፍር ገዛኽኝ

addiszemen
1