1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
admin@hebrezema.info
የጥቁር ከዋክብቶች ነፀብራቅ በጋቦን ሰማይ ስር በአዲስ ታሪክ
January 11, 2017
የወንድማማችነትን መንፈስ በአፍሪካውያን መካከል ማጠናከርና የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግሉን ማበረታታት ዓላማው አድርጎ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ግብፅና ደቡብ አፍሪካ መስራችነት
እ ኤ አ በ1950ዎቹ የተጀመረው የአፍሪካ ዋንጫ፤ ከዓመት ዓመት እያደገ ተወዳጅነቱ እየጨመረ ዛሬ በዓለማችን ላይ ከሚካሄዱ ምርጥ አህጉራዊ የእግር ኳስ መድረኮች
አንዱ ለመሆን በቅቷል።

የአፍሪካ ዋንጫን መመልከት በስታዲየም ተገኝቶ አሊያም በቴሌቪዥን መስኮት እግር ኳስን መመልከት ብቻም አይደለም። ሌሎች አስደማሚ ሁነቶችም በመድረኩ ጎልተው
ይደምቃሉ። በስታዲየም እዚህም እዚያም ጎልተው የሚታዩ ህብረ ቀለማት፤ከአራቱም ማዕዘን ጎልተው የሚሰሙ የድጋፍ ድምፆችና ማራኪ ጭፈራዎች፤ የመድረኩ ድባብ
አድማቂዎች ሆነው መድረኩን ያስውቡታል።
አፍሪካውያን ለእግር ኳስ ያላቸው ፍቅርና ክብር እጅጉን የላቀና ከመዝናኛነቱም አልፎ ከዕለት ኑሯቸው ጋር የተቆራኘ ነው። አህጉሪቱም በኳስ ፍቅር ያበዱ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ
ክለባቸውን እንዲሁም ብሄራዊ ቡድናቸውን የሚያበረታቱ የሜዳው ድባብ አድማቂ የሆኑ ምርጥ ደጋፊዎች አሏት።

አህጉሪቱ የምርጥ ደጋፊዎች እንብርት የመሆኗን ያህል የምርጥ ተጫዎቾች ባለቤትም ነች። ከልጅነት ጀምሮ በየመንደሩ ባዶ እግራቸውን እግር ኳስ የሚጫወቱ፤በልበ
ሙሉነት ራሳቸውን ለእግር ኳስ ፍቅር አሳልፈው የሰጡ፤ ለእግር ኳስ ፍቅር የሚታመኑ ተጫዋቾችም የአህጉሪቱ ሀብቶች ናቸው። በድንቅ እግር ኳሳዊ ጥበብ ችሎታ የተካኑ
በሙያቸው ብዙዎችን ከመቀመጫቸው አስነስተው ማስጨብጨብ የቻሉና ከአህጉሪቱም ተሻገረው በታላላቅ ሊጎች ድንቅ ችሎታቸውን ያስመሰከሩ ጥበበኞችም አሏት። እነዚህ
ጥበበኞችም ድንቅ የእግር ካስ ጥበብ ልህቀታቸውን ከሚያሳዩባቸው መድረኮች መካከልም አንዱም በአህጉሪቱ በሚገኙ አገራት መካከል የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ መድረክ
አንዱ ነው።

ዘንድሮም መድረስ አይቀርምና በናፍቆት ሲጠበቅ የነበረው በአልሸነፍ ባይነት የዓላማ ፅናት ላይ ያነጣጠረ የፍልሚያ፣የፉክክር መድረክ የሆነው አጓጊው የአፍሪካ ዋንጫ እነሆ
ደርሷል። ዘንድሮ በጋቦን አስተናጋጅነት የሚካሄደው ይህ 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 16 ሀገሮችን በአንድ መድረክ ሊያፋልም በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ቀርተውታል።

በመድረኩ አገራት በእግር ኳስ ይወዳጃሉ። ከማንም ሊሰወር የማይችል ፋና በጋራ ለኩሰው አንድነትን ከፍ አድርገው በኩራት ይቆማሉ። የታላላቅ ስምና እግር ኳስ ችሎታ
ባለቤት የሆኑ በእያንዳንዷ ደቂቃ ዓላማቸው ላይ ያነጣጠሩና በራሳቸው አቅም የእግር ኳሱን የአሸናፊነት አቅጣጫ የመቀየር አቅም ያላቸው ተጫዋቾችም ለአሸናፊነት
ይፋለማሉ።

የጋቦኑ መድረክ በአህጉራቸው በሚጫወቱ አፍሪካውያን ተጫዋቾች የእርስ በእርስ እግር ኳሳዊ ጥበብ ትዕይንትና የአልሸነፍም ባይነት ትግል ብቻ አይታጠርም። በትንሹ 20
የሚሆኑ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እንዲሁም ከሌሎች ሊጎች የሚጫወቱ ምትሐታዊ የኳስ ጥበብ የተካኑ ተጫዋቾችም የፍልሚያው ታዳሚ ይሆናሉ።

ማንኛውም ተጫዋች ይሁን አገር በአፍሪካው ዋንጫ መድረክ መገኘት የሚያጎናፅፈውን ክብርና የሚሰጠውን የተለየ ስሜት ጠንቅቆ ያውቀዋል። ይሁንና በዚህ ታላቅ መድረክ
ከመገኘትም ባለፈ በመድረኩ አዲስ ታሪክ መሥራት የሁሉም ህልምና ምኞት ነው። በ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አፍሪካውያን ኮከቦች በጋቦን ሰማይ ለማንፀባርቅና በመድረኩ
አዲስ ታሪክ ለመሥራት ጥርሳቸውን ነክሰው የውድድሩን መጀመር የሚያበስረውን ፊሽካ በጉጉት መናፈቅ ጀምረዋል።

በአፍሪካ ዋንጫው ታሪክ 15 ዋንጫዎችን በጋራ የጠራረጉት ግብፅ፤ጋናና ካሜሮን በተጓዷኝ የአልጄሪያ የቱኒዚያ የሞሮኮ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ኮትዲቯር ብሄራዊ
ቡድኖች ዋንጫውን ከሳሙ አገራት መካከል ስማቸው አብሮ ይነሳል። እነዚህ አገራት ታዲያ ዘንድሮ በጋቦኑ መድረክ አዲስ ታሪክ ለመሥራት ፊት ለፊት ተፋጠዋል። በዚህ
ዋንጫ ፍልሚያ ስምንት የምዕራብ አፍሪካ አገራት የሚታደሙ ሲሆን፣ ይህም በአህጉሪቱ እግር ኳስ ስማቸውንና ተሳትፋቸውን ከማናም በላይ ማጉላት እንደቻሉ አሳይቷል።

ሰሜን አፍሪካዎቹ ግብፅ፤ቱኒዚያ አልጄሪያና ሞሮኮ ግን ብዛት ሳይሆን ጥራት ብለው አቋም ይዘዋል። በርካታ ጨዋታ በማድረግና ከማንም ብሄራዊ ቡድን በላይ ጨዋታዎችን
በማሸነፍ ሰባት ጊዜ ዋንጫውን በመሳም የሚስተካከላቸው የሌላው ፈርኦኖቹ ምንም እንኳን ባለፉት ሦስት ውድድሮች በመድረኩ ባይታዩም፤ አሁን ላይ ዳግም ወደ ንጉሱነት
መድረክ ተመልሰዋል። የምንጊዜም የክብር የበላይነታቸውን አስጠብቀው የጋቦኑን መድረክ በግርማ ሞገስ ይረግጣሉ።

በአሰልጣኛቸው ሄክተር ኮበር የሚመሩት ፈርኦኖቹ፤ በወጣትና ድንቅ ችሎታ ባለቤት በሆኑት በመሃመድ ሳላህ፤ ረመዳን ሳሆቢና የአርሰናልን ቤት የመሃል በር በአግባቡ
በመዝጋት በሚታወቀው መሃመድ ኤልኔኒ ብቃት እየተገዙ ዳግም አዲስ ታሪክ ለመሥራት በጋቦን ሰማይ ስር ለመጻፍ የውድድሩን መጀመር በጉጉት ከሚጠበቁት ብሔራዊ
ቡድኖች መካከል ይገኙበታል።

በጋቦኑ መድረክ የውጭ አሰልጣኞች ይጎሉበታል። በመድረኩ ከተገኙት 16 ቡድኖች መካክል በምዕራባዊያን አሠልጣኝ የማይሠለጥኑት ሦስቱ ብቻ ናቸው። ቀሪዎቹ 13
ክለቦች የሚመሩት በውጭ አገር አሠልጣኞች አሊያም የአገሬው ተወላጅ ባልሆኑት ነው። ምንም እንኳ አሁን ላይ ምዕራባዊያን አሠልጣኞች ይነገሡበት እንጂ በመድረኩ
ታሪክ ቀደም ባሉት ዓመታት የአገሬው አሠልጣኞች የበላይነትም ይጎላ ነበር። አስራ አንድ የሚሆኑ አሠልጣኞችም ዋንጫውን የግላቸው ማድረግ የቻሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ
መካከል ግብፃዊው ሁሴን ሺሃታና እና ጋናዊው ቻርለስ ጉሜ ካያፊ እያንዳንዳቸው ሦስት ጊዜ ዋናጫ በመውሰድ የሚስተካከላቸው የለም።

በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫም ፈረንሳዊው ሀርቬ ሬናልድ የዋንጫ ረሃብ የጠማቸው ሰሜኖቹን ሞሮኮዎችን በፊት አውራሪነት አስከትሎ ይደርሳል። ሦስተኛ ዋንጫውን
በማንሳት ከግብፁና ከጋናው አሠልጣኝ እኩል የሚያደርገው አዲስ ታሪክ ለመጻፋም ሸሚዙን ሰብስቧል። ለዚህም ከቀድሞ ክለቦቹ ጋና እና ኮትዲቯር ተጫዋቾች ጋር
ይተናነቃል።

በአፍሪካ ዋንጫው ታሪክ ግብፅ እና ጋናን የመሳሰሉ አንዳንድ አገራት ከመድረኩ ጋር በእጅጉ ይወዳጃሉ። ይዋደዳሉ። ውድድሩን ይውዱታል ቤተኛም ናቸው እስኪባል
ተሳትፏቸው አስገራሚ ነው። ይሁንና ከእነዚህ አገራትም በላይ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የቱኒዚያን ያህል ከመድረኩ ጋር የተዋደደ የተፋቀረና መድረኩን የተመላለሰበት
ማግኘት ከባድ ነው። ለቱኒዚያዎች የጋቡኑ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏቸው ከ1994 ጀምሮ በተሳተፉባቸው ተከታታይ መድረኮች አሥራ ሁለተኛ ነው።

በእነዚህ ዓመታት በ1996 ለፍፃሜ መድረስ ቢችሉም ዕድል ከእነርሱ ጋር አልነበረችም። ይሁንና ከስምንት ዓመታት በኋላ ዕድል ፊቷን ወደ እነርሱ አዙራላቸው
ዋንጫውንም አግኝተዋል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ግን ስምንት ውስጥ መቀላቀል እንኳን አልቻሉም። ዘንድሮ ይህ ታሪክ መለወጥ እንዳለበት ከአገሬው ደጋፊና ተጫዋቾች በላይ
በተደጋገሚ ሲገልጽ የተሰማ የለም። እናም ቱኒዚያውያን ከታሳትፎም በላይ ዋንጫ ወደ አገራቸው ይዘው ለመመልስ ቆርጠው ነው ጋቦን የደረሱት።

እንደ ቱኒዚያ ሁሉ በርካታ ብሔራዊ ቡድኖች መድረኩን ተመላልሰው ቢፋለሙበትም አንዳንዶች በአንፃሩ ዓይናችሁን ለአፈር የተባሉ በሚመስል መልኩ የፍልሚያውን ክልል
ዘልቀው መርገጥ አልቻሉም። በአህጉሪቱ ከከተሙ አገራት መካከል15 የሚሆኑት እስከአሁን መድረኩን አያውቁትም። ምንም እንኳን በእርስ በእርስ ጦርነት የምትታመሰውና
ከተመሰረተች በጣት የሚቆጠር ዓመት ያስቆጠረችው ደቡብ ሱዳን በመድረኩ አለመሳተፏ ብዙም ባያስገርምም የቡሩንዲ፤ ጋምቢያ፤ ቻድ፤ሳኦቶሜና ፕሪንስፔ በመድረኩ
አለመታያት ግን ሁሌም አግራሞትን ያጭራል።

ይሁንና አንድ ነጥብ 7 ሚሊዮን ህዝብ ያላትና በታሪኳ በአገራት የእግር ኳስ ደረጃ ሰንጠረዥ 100 ውስጥ ገብታ የማታውቀው ጊኒ ቢሳው እንዲሁም ከአፍሪካው ዋንጫ
መድረክ ተራርቀው የቆዮት የዙምባብዌ ኮከቦች በጋቦን ሰማይ ስር ሳይጠበቁ ለማንፀባረቅ የሚያግዳቸው እንደሌለ በመናገር ላይ ይገኛሉ።

በአፍሪካው ዋንጫ ታሪክ በርካታ የማይታመኑ ደስታና ኀዘን ያስከተሉ ውጤቶች፤ ክስተቶች ታይተዋል። አንዳንዶች ለአሸናፊነትም ይሁን ዋንጫውን ለመሳም በመታደላቸው
በደስታ ጮቤ ሲረግጡ አንዳንዶች በአንፃሩ ዋንጫውን ለመሳም ተቃርበውም ቢሆን ዕድል ፊታቸውን አዙራባቸው የሽንፈትን ፅዋ ሳይወዱ በግድ ተጎንጭተዋል።

በዋንጫው ታሪክ በመጨረሻ ጨዋታ በመሸነፍ በዋንጫ ማጣት የተሰቃዩት ግን የጥቋቁር ኮከቦቹን የቀድሞና የአሁን ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች አዩማ ቤተሰቦች
የሚስተካከላቸው የለም። ራሂም፤ አንድሬና ጆርዳን አዩ በመጨረሻ የዋንጫ ጨዋታ በግብፅ፤ በኮትዲቯር በመሸነፍ ዋንጫ የማጣት ህመምን ታመዋል። አባት አቢዲ ምንም
እንኳ በ1982 ዋንጫውን ከፍ አድርጎ መሳም ቢችልም፤እንደ ልጆቹ ሁሉ በ1992 ዓ.ም በመጨረሻ ጨዋታ ተሸንፎ ድሉን ተቀምቷም፤ የሽንፈትን ፅዋም እየመረረውም
ቢሆን ተጎንጭቷል።

የአፍሪካ ዋንጫውንም አራት ጊዜ በመሳም የሚታወቁትና አምስተኛውንም ለማንሳት አቅም እንዳጠራቸው በተደጋጋሚ የሚስተዋሉት ጥቋቁሮቹ ኮከቦች ዘንድሮ በዋንጫ ረሃብ
አያፋሸጉ ዋንጫ በማጣት ለመታማም ፍላጎት የላቸውም። ጋቦንም የአምስተኛ ዋንጫቸው ትክክለኛው የታሪክ መጻፊያ ቦታ መሆኑን አምነው እስከመቀበል ደርሰዋል። አንድሬና
ጆርዳን አዩም የአገራቸውን ብሔራዊ ቡድን ለክብር ከማብቃትም በላይ የዋንጫ ማጣት ጥማቸው የሚቋጨው ጋቦን ሰማይ ስር መሆኑን ከወዲሁ መናገር ጀምረዋል።

ለረጅም ዓመታት በሎረንስ ፖኮ 14 ግቦች ተይዞ የቆየው የአፍሪካው ዋንጫ የምንጊዜም ግብ አስቆጣሪነት ክብረ ወሰን አሁን ላይ በካሜሮናዊው የተከላካዮች ጭንቀትና የፊት
መስመር አዳኝ ሳሙኤል ኤቶ የተያዘ ነው። ካሜሮናዊው የግብ አዳኝ በተሳተፈባቸው ስድስት የዋንጫ መድረኮች በአጠቃላይ 18 ግቦችን ከመረብ በማዋሃድ ነው ክብረ ወሰኑን
የግሉ ያደረገው። ይሁንና ይህ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብረ ወሰን በሳሙኤል ኤቶ ስም እስኪጻፍ 30 ዓመታትን መታግስ ግድ ብሏል።

ይሁንና አሁንም ቢሆን ላለፉት አራት አስርት ዓመታት ያልተሰበረ በአንድ የአፍሪካ ዋንጫው መድረክ በርካታ ግብ በማስቆጠር የተያዘው ክብረ ወሰን አለ። ይህም ክብረ ወሰን
በ1974 ውድድር ሙላምባ ናዳይስ በተባለ ተጫዋች ስም የተጻፈ በአንድ መድረክ 9 ግቦችን የማስቆጠር ክብረ ወሰን ሲሆን፤ ታሪኩም ዓመታትን ተሻግሮም ቢሆን
የሚሰርዘው አላገኘም። ዝንድሮም ይህ ታሪክ ሌሎች ዓመታት ይጠብቅ ይሆን? ጥቋቁር ኮከቦች የሚንጸባረቁበት የጋቦን መድረክ ለሁሉም ታሪኮች ቀጣይነት አሊያም አዲስነት
መልስ ይኖረዋል።

ታምራት ተስፋዬ
addiszemen
1