መቶ አለቃ አበያ በቀለ በልጆቻቸው ስም የሶስት ሺ የአሜሪካን ዶላር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዢ ፈጸሙ

July 15,2021

ቀደም ሲል በኢትዮጵያ አየር ኃይል የውጊያ አውሮፕላን አብራሪ የነበሩት እና አሁን የስቶክሆልም ከተማ ነዋሪ የሆኑት መቶ አለቃ አበያ በቀለ በልጆቻቸው ስም (በሞኢቦን፣ ኒሞና እና ሐወኒ) የሶስት ሺ የአሜርካን ዶላር (አሁን ባለው ምንዛሪ መጠን 134,640.00 ብር) የህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዢ ፈጽመዋል።


በወቅቱ መቶ አለቃ አበያ ባስተላለፉት መልዕክት በስሙ ለሚጠሩት አባይ ድጋፍ ሲያደርጉ በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት መሆኑን ገልጸው ልጆቻቸውም ሀገራዊ ስሜት እንዲያድርባቸው እና በዚህ ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት አማካኝነት ከሀገራቸው ጋር እንዲተሳሰሩ በማሰብ እንደሆነ አስረድተዋል።


በተጨማሪም በኖርዲክ ሀገራትና በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን የሀገር ኩራትና የሉዓላዊነታችን ምልክት ለሆነው ለህዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ እና በተለይም ልጆቻቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ትስስር እንዲጠናከር በስማቸው ቦንድ እንዲገዙ ምክራቸውን ለግሰዋል።


መቶ አለቃ አበያ በቀለ አያይዘውም ሀገራችን በአሁኑ ጊዜ የውስጥ እና የውጭ ስጋቶች የተጋረጡበት ጊዜ በመሆኑ በግላቸው ባላቸው ሙያ ከሀገራቸው ጎን መሆናቸውን ጠቅሰው ሌሎችም የዳያስፖራ አባላት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ከሀገራቸው ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፈዋል። የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በመጀመሩ በኖርዲክ ሀገራት ውስጥ ከፍተኛ መነሳሳት የተስተዋለ ሲሆን ሁለተኛ ዙር ሙሌት ከተጀመረ ወዲህ አስር ሺ የአሜርካ ዶላር የሚጠጋ የቦንድ ሽያጭ ተፈጽመዋል።


ክቡር አምባሳደር ድሪባ ኩማ መቶ አለቃ አበያ ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላቅ ያለ ምስጋና በማቅረብ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን እና ተውልድ ኢትዮጵያዊያን የእሳቸውን አረዓያ በመከተል ሁለተኛ ሙሌት እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ለህዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ እና በሀገራችን ላይ የተቃጣውን የውስጥና የውጭ ስጋት ከመቀልበስ አኳያም ሁሌንተናዊ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።


Spokesperson Office of the Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia Ethiopian Diaspora Agency