1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ወዴት እያመራ ነው?
January 30, 2017
ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል የደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባን ያልረገጡት የተቃዋሚ ቡድኑና የኑዌሮች መሪ ዶ/ር ሪክ ማቻር ጁባ እንደሚገቡ
ሲገለጽ፣ ለደቡብ ሱዳን ችግር መፍትሔ ለመሻት ተስፋ ፈንጥቆ ነበር፡፡ በነሐሴ ወር 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተደረገ ስብሰባ ሁለቱ
የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች ባደረጉት የሰላም ስምምነት መሠረት፣ ተቃዋሚው የሱዳን ሕዝቦች ነፃ አውጭ ጦር አመራር ወደ ደቡብ ሱዳን
ለመግባት ወስኖ ነበር፡፡

ይህ የአዲስ አበባ የሰላም ስምምነት በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና ዓለም አቀፍ አጋሮቹን ያቀፈው ኢጋድ ፕላስ
ካደረጓቸው በርካታ የማደራደር ጥረቶቹ አንዱ ነበር፡፡ ከአፍሪካ አገሮች ሁሉ በዕድሜ አነስተኛ የሆነችው ደቡብ ሱዳን እ.ኤ.አ. ከታኅሳስ
2013 ጀምሮ ደም አፋሳሽ በሆነ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ የቆየች ሲሆን፣ ይህንን ግጭት ለማስቆም የተለያዩ አካላት የተለያዩ ጥረቶች
ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባውን የሰላም ድርድር ለመሩት የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሥዩም መስፍንና ለሌሎች አደራዳሪዎች ሒደቱ እጅግ ፈታኝ
ነበር፡፡ በሥልጣን ላይ ያሉት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር፣ ተቀናቃኛቸው ዶ/ር ሪክ ማቻር ስምምነቱን ከፈረሙ ከሳምንት በኋላ ነበር
የፈረሙት፡፡ ስምምነቱ በከፍተኛ ተፅዕኖና ጥረት ቢፈረምም፣ ከሱዳን ለመገንጠል በጋራ የተዋጉት የዲንቃና የኑዌር መሪዎች ለገቡበት ስሜት
አልባ ግጭት ዕረፍት የሚሰጥ ነው ተብሎ ታምኖበት ነበር፡፡

የነሐሴው የአዲስ አበባ ስምምነት የሁለቱ ወገኖች ሥልጣን ክፍፍል ቀመርን ሁሉ የያዘ ለየት ያለ ስምምነት ነበር፡፡ በዚህም መሠረት የኪር ቡድን
53 በመቶ የሚሆነውን የካቢኔ ወንበር እንዲይዝ፣ የዶ/ር ማቻር ቡድን ደግሞ 33 በመቶ እንዲይዝ፣ ግጭቱ ሲፈጠር እንድታሰሩ የተደረጉት
ፖለቲከኞች ቡድንና ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ ሰባት ሰባት በመቶ እንዲይዙ ተወስኖ ነበር፡፡ ስምምነቱ ኪር ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲቆዩ፣
ዶ/ር ማቻር ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሆኑና የኢኳቶሪያል ክልል ተወካይ ጄምስ ዋኒ ኢጋ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሆኑም ያስቀምጣል፡፡

በስምምነቱ መሠረት የተፈጠረው የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ አንድነት መንግሥት መዋቅር ለሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች ተመራጩ መፍትሔ
አልነበረም፡፡ ይሁንና የነበረውን ግጭት ለማስቆም የተሻለ አማራጭ አልነበረም፡፡ ስምምነቱ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ዶ/ር ማቻር ጁባ
መግባታቸው የግድ ነበር፡፡

በድርድሩ ወቅት ከነበሩበት ኢትዮጵያ ወደ ጁባ ለማቅናት ዶ/ር ማቻር ስምምነቱ ከተፈጸመ በኋላ ስድስት ወራትን ጠብቀዋል፡፡ ይህን ያስገደደው
በወቅቱ በጁባ የነበረው የፀጥታና የደኅንነት ሁኔታ ነበር፡፡ ይህን የተገነዘበው ክልላዊው አደራዳሪ ቡድን ኢጋድ ከተማዋን ከሁለቱ ተቀናቃኝ
ወታደሮች እንቅስቃሴ ነፃ ለማድረግ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ ይሁንና ተቀባይነት አላገኘም፡፡

በዚህም የተነሳ ኢጋድ በጁባ ያለውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለመቀበል ተገዶ ነበር፡፡ ነገር ግን ፕሬዚዳንት ኪር በሥልጣን ላይ እያሉ ዶ/ር ማቻር
ምን ያህል የፀጥታ ኃይል ይዘው ጁባ ይገባሉ የሚለው ጉዳይ ስምምነት የሚጠይቅ ነበር፡፡ ዶ/ር ማቻር ጁባ ለመግባት መነሻቸውን ከጋምቤላ
ኤርፖርት ሁለት ጊዜ ሰርዘውም ነበር፡፡

ከሰላም ስምምነቱ በኋላ እዚህም እዚያም መጠነኛ ግጭቶች ሪፖርት ቢደረጉም፣ ደቡብ ሱዳን ለወራት አንፃራዊ ሰላም አግኝታ ነበር፡፡ ይህ ግን
በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተፈጠረው ግጭት ተቋርጧል፡፡ ሁለቱ ተቀናቃኝ መሪዎች በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ውይይት እያደረጉ ባሉበት
ተመሳሳይ ወቅት እ.ኤ.አ. ጁላይ 8 ቀን 2016 የሁለቱ መሪዎች የፀጥታ ኃይሎች ከውጭ እየተጋጩ ነበር፡፡ በግጭቱ ከ150 በላይ ሰዎች
ከሁለቱም ወገን ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ዶ/ር ማቻር ወደ ካምፓቸው ለመመለስ ጥበቃ የተደረገላቸው በኪር የፀጥታ ኃይሎች ነበር፡፡

ይህ የቤተ መንግሥት ክስተት ሌላ አውዳሚ ግጭትን መጋበዙ ብቻ ሳይሆን፣ ሁለቱ መሪዎች የፀጥታ ኃይሎቻቸውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠርና
ማዘዝ እንደማይችሉም ለዓለም ገሃድ አውጥቷል፡፡ ሁለቱም መሪዎች ግጭቱን ቢያወግዙም ሌላ ተመሳሳይ ግጭት እንዳይፈጠር ግን መከላከል
አልቻሉም፡፡ ከቤተ መንግሥቱ ግጭት በኋላ ባሉት ጥቂት ቀናት በጁባ ከ500 ሰዎች በላይ ሕይወታቸውን ያጡበት ሌላ ግጭት ተፈጥሯል፡፡ በዚህ
ግጭት ኑዌሮች፣ የውጭ ዜጎች፣ የተመድና የዕርዳታ ድርጅቶች ሠራተኞች ዒላማ በመሆናቸው የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የፈጸሙት ጥቃት
እንደሆነ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡

ግጭቱ የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱን ወታደራዊ መቀመጫ ሙሉ በሙሉ አውድሟል፡፡ በዚህም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሔሊኮፕተር
እየታገዙ ለሳምንት እንዲከታተሏቸው አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ዶ/ር ማቻር የኮንጎን ድንበር ሲሻገሩ በመልካም ጤንነት ላይ ያልነበሩ
በመሆናቸው የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነበር፡፡

ፕሬዚዳንት ኪር በዋነኛው ተቃዋሚ ዶ/ር ማቻር የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደርጎብኛል የሚል ክስ ማቅረባቸውና እስከ ቀጣይ ምርጫ
ባሉበት በስደት እንዲቆዩ ማሳሰባቸው ይበልጥ ሁኔታዎችን አወሳስቧል፡፡

ኪር በተጨማሪም ከኑዌር ጄኔራሎች ብዙም ድጋፍ እንደሌላቸው የሚነገርላቸውን ጄኔራል ታባን ዴንግን በቋሚነት ዶ/ር ማቻርን ተክተው ተቀዳሚ
ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ አደረጉ፡፡ መጀመሪያ ላይ ጄኔራል ታባን ራሳቸው ቦታውን የሚይዙት ዶ/ር ማቻር ሁኔታዎች ፈቅደውላቸው ወደ
ጁባ እስኪመለሱ ድረስ እንደሆነ ገልጸው ነበር፡፡ የኢጋድ አባል አገሮች አቋምም ከዚህ ብዙ የተለየ አልነበረም፡፡

ነገር ግን የዶ/ር ማቻር መመለስ ተስፋው እየደበዘዘ ሲመጣ ጄኔራል ታባን ከኑዌር ያላቸውን ድጋፍ እያጠናከሩ፣ በዓለም አቀፍ መድረኮችም
ደቡብ ሱዳንን በመወከል መቅረብ ጀመሩ፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል በሰላም ስምምነቱ መሠረት የብሔራዊ አንድነት መንግሥትን ማቋቋም ይቻላል ወይ
የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነበር፡፡

ከዚህ በኋላ የሰላም ስምምነቱ ያስቀመጠው የሽግግር ሒደት እክል ገጥሞት እንደቆመ ግን ግልጽ ሆነ፡፡ የፖለቲካ ተንታኝና የአፍሪካ ቀንድ
ኤክስፐርት ዶ/ር መሐሪ ታደለ ማሩ ሁለቱ ተቀናቃኝ መሪዎች ፕሬዚዳንት ኪርና ዶ/ር ማቻር የደቡብ ሱዳንን የሰላም ሒደት ለማረጋገጥ
እንደማያስችሉ፣ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት የስልክ ቃለ ምልልስ ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር መሐሪ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ኪር ዶ/ር ማቻር አለመኖራቸውን በመጠቀም ጄኔራል ታባንን መተካታቸው ስህተት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
‹‹ኑዌሮች መሪያቸውን የመወሰን ቁርጠኝነት አላቸው፡፡ ለእነሱ መሪያቸው ዶ/ር ማቻር ናቸው፤›› በማለትም፣ ‹‹በኑዌሮች ዘንድ ያላቸውን
የድጋፍ መሠረት ለማጠናከር እየሞከሩ ቢሆንም፣ ይህን ድጋፍ በአጥጋቢ ሁኔታ ጄኔራል ታባን ያገኛሉ ብዬ አላምንም፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

የኑዌርና የዲንቃ ግጭት ግን አውራው የደቡብ ሱዳን ችግር ይሁን እንጂ፣ በአገሪቱ ፖለቲካ ሌሎች አካላትም አሉ፡፡ ቡድን አሥር በመባል
የሚታወቀው የቀድሞ የፖለቲካ ታሳሪዎች ቡድን አባላት በእርስ በርስ ጦርነቱ ዘመን በአገሪቱ ፖለቲካ ቁልፍ የአመራር ሚና የነበራቸው ሲሆኑ፣
በቀድሞው የሱዳን ሕዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ ዋና ጸሐፊ ፓጋን አሙም ኦኪያች ይመራሉ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2013 በኋላ በግጭቱ ጉልህ ሚና
መጫወት ጀምረዋል፡፡ አሙምና ሌሎች ፖለቲከኞች በፕሬዚዳንት ኪር ታስረው የነበረው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድርገዋል ተብለው ነው፡፡

ይህ የፖለቲካ እስር እ.ኤ.አ. በ2013 ለተጀመረው ጦርነት እንደ መነሻ ይቆጠራል፡፡ እነዚህ ፖለቲከኞች ታስረው ከተፈቱ በኋላ
ተቃውሟቸውን ያለ ኃይልና ጦርነት ለማሰማት ሲጥሩ ነበር፡፡

የቡድን አሥር አስተባባሪ ዶ/ር ሲሪም ሂቴንግ ኦፍሆ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የደቡብ ሱዳን ፖለቲካ የኑዌርና የዲንቃ ጉዳይ
ተደርጎ መወሰዱ ስህተት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ዲንቃና ኑዌር ቢደመሩም አብላጫ አይሆኑም፡፡ በአገሪቱ 64 ብሔሮች አሉ፡፡ ነገር ግን የሁሉም
ትኩረት በሁለቱ ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር ኦፍሆ በደቡብ ሱዳን ሦስተኛው ትልቁ ብሔር ከሆነው ከኢኳቶሪያ ክልል የመጡ ሲሆን፣ ሌሎች ብሔሮች በኑዌርና በዲንቃ ጉዳይ
ትዕግሥታቸው እየተሟጠጠ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ቡድን አሥር ራሱ ወደ ጦርነት ሊገፋ እንደሚችልም አስጠንቅቀው ነበር፡፡

ዶ/ር መሐሪም ፕሬዚዳንት ኪር ከኢኳቶሪያ ክልል ተቃውሞ ሊገጥማቸው እንደሚችል ይስማማሉ፡፡ የደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ራሷ
በኢኳቶሪያ ክልል የምትገኝ በመሆኑ፣ አገሪቱን ለመምራት የኢኳቶሪያ ድጋፍ የግድ እንደሚል ጠቁመዋል፡፡ አካባቢው በቀደሙ ጊዜያት
ለፕሬዚዳንት ኪር ድጋፍ ይሰጥ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በሐምሌ ወር 2016 ደግሞ ግጭት ካገረሸ በኋላ ኢጋድ ፕላስን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ትዕግሥቱ
እያለቀ ይመስላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማምጣት ኢጋድ እያደረገ ያለው ጥረት ባገረሸው ጦርነት
ምክንያት እክል እንደገጠመው በቅርቡ ገልጸዋል፡፡

የነሐሴ ወር 2007 ዓ.ም. የአዲስ አበባው ስምምነት እክል ከገጠመው ኢጋድ ጉዳዩን ለአፍሪካ ኅብረትና ለተመድ እንደሚመራው ስምምነቱ
ይገልጻል፡፡ አሁን ሒደቱ እክል እንደገጠመው ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ለመጣል የቀረበው
ሐሳብ እንደ ጃፓንና ሩሲያ ያሉ አገሮች በመቃወማቸው አልተሳካም፡፡

አካባቢያዊ የፀጥታ ኃይሎች ጥበቃ በ4,500 ወታደሮች እየተሰጠ ያለው እንደ ኢትዮጵያና ኡጋንዳ ካሉ በጎ ፈቃደኛ አገሮች ተውጣጥቶ ነው፡፡
ይህ ሊሆን የቻለው የኪር አስተዳደር የውጭ ወታደሮች በደቡብ ሱዳን መሰማራት አይችሉም በማለቱ ነው፡፡ እንደ ዶ/ር መሐሪና ሌሎች ተንታኞች
ገለጻ አካባቢያዊ የጥበቃ ኃይሉ ላይ እንደ ተመድ፣ አፍሪካ ኅብረትና ኢጋድ ያሉ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አካላት የተስማሙበት አይደለም፡፡

የዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ በድርጊትና በዝምታው ለጄኔራል ታባንና ለኪር አስተዳደር ድጋፍ እየሰጠ ነው በሚልም ይታማል፡፡ ዶ/ር መሐሪ
በኑዌሮች ዘንድ ዶ/ር ማቻር ያላቸውን ድጋፍ በመጥቀስ፣ ይህ ለአገሪቱ የሰላም ሒደት ትልቅ ተግዳሮት ሊፈጥር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡

ከዚህ በተቃራኒ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የፀጥታ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪና ኤክስፐርት የኢጋድ አባል አገሮች ዶ/ር ማቻርን
በመተው ለጄኔራል ታባን ድጋፍ በማድረግ ለሰላም ሒደቱ ዕድል ከመስጠት የዘለለ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ተከራክረዋል፡፡ ‹‹አሁን
ፕሬዚዳንት ኪርና ዶ/ር ማቻር ዓይን ለዓይን እንኳን መተያየት አይችሉም፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ዶ/ር ማቻር ኡጋንዳን ባስቆጣ ሁኔታ ከተቃዋሚው ሎርድስ ሬዚስታንስ አርሚ ጋር መሥራታቸውና በእርስ በርስ ጦርነቱ ጊዜ
ከሱዳን መንግሥት ጋር ለአጭር ጊዜም ቢሆን መሥራታቸው፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ብዙም እምነት እንዳይጣልባቸው አድርጓል፡፡ እንደ
ኤክስፐርቱ ገለጻ ኢጋድና ክልላዊ ተቋማትም ይህን ይጋራሉ፡፡

በቅርቡ የኪር አስተዳደር ኢትዮጵያን የሚጎዳ ስምምነት ከግብፅ ጋር ፈጽሟል በሚል ሪፖርቶች መውጣታቸው ይታወሳል፡፡ የፀጥታ ጉዳዮች
ኤክስፐርቱ ግን ይህን ለመቀበል ይቸገራሉ፡፡ ደቡብ ሱዳን በየትኛውም መሥፈርት ይህን ልታደርግ እንደማትችልም ተከራክረዋል፡፡ ‹‹እርግጥ ነው
በፀጥታው ምክር ቤት ቀርቦ የነበረውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ የማድረግ ምክረ ሐሳብ ውድቅ ለማድረግ ግብፅ ድምፅ ስለሰጠቻት ውለታ
አለባት፤›› ያሉት ኤክስፐርቱ፣ በአካባቢው የጥበቃ ኃይል መሰማራት ደቡብ ሱዳንና ግብፅ ደስተኛ አለመሆናቸውም ሌላኛው የጋራ ጉዳይ
እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ግብፅ በሚታወቅ ምከንያት የኢትዮጵያ ወታደሮች በደቡብ ሱዳን መሰማራታቸውን ልትቀበል አትችልም፤›› ብለዋል፡፡

ይሁንና ዶ/ር መሐሪ የተባለው ስምምነት ተፈጽሟል ቢባል እንኳን ኢትዮጵያን ሊያስደንቅ እንደማይገባ ይሞግታሉ፡፡ ከዚህ አንፃር እንደ
ኤርትራና ሶማሊያ ሁሉ ደቡብ ሱዳን ቀጣይዋ የግብፅ ግንባር እንደምትሆን ይጠበቃል፡፡
admin@hebrezema.info
1