1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
ኬኛ ቤቬሬጅስ አክሲዮን ማህበር ተመሰረተ
April 2, 2017
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኬኛ ቤቬሬጅስ የተሰኘ ግዙፍ አክሲዮን ማህበር በግል ባለሀብቶች፣ በህዝብና በመንግስት
ጥምረት ዛሬ በይፋ ተመስርቷል።

ይህ ኩባንያ ከአልኮል ነጻ የሆኑ የማልት መጠጦች፣ ለስላሳ መጠጦች፣ ጭማቂዎች፣ የማዕድን ዉሃ፣ የብርጭቆና የጠርሙስ ፋብሪካዎችን እና
የስፖርት እና መዝናኛ ዘርፍን ያካተተ ሲሆን ኬኛ ቢራንም ያመርታል።

የኦሮሚያ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ እንዳስታወቀው ለኩባንያው እውን መሆን 5 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ካፒታል እንደሚያስፈልግ በጥናት
ተረጋግጧል።

ከዚህ ውስጥ የመንግስት የልማት ድርጅቶች 15 በመቶ ብቻ ድርሻ እንደሚኖራቸው ተገልጿል።

መንግስት ይህን ድርሻ የሚይዘው በዋናነት ከዚህ ቢዝነስ ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን የክልሉ ባለሀብቶች ከወጣቶችና አርሶ አደሮች ጋር
ተቀናጅተው መስራት እንዲችሉ ለማነሳሳት ነው ብለዋል የቢሮው ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ።

ቀሪው የአክሲዮን ድርሻ በግል ባለሀብቶች፣ በወጣቶች እና በአርሶ አደሮች የሚሸፈን ይሆናል።

በዛሬው ዕለት በኦሮሞ ባህል ማዕከል አዳራሽ ብቻ በተደረገ የምስረታ ስነ ስርዓት የ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር አክሲዮን ተሽጧል፡፡

ዛሬ ከተሸጠው አክሲዮን የመንግስት የልማት ድርጅቶች የ500 ሚሊየን ብር፣ በመላው ኦሮሚያ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የተደራጁ
ወጣቶች የ300 ሚሊየን ብር አክሲዮኖች የገዙ ሲሆን፥ የቀረውን አክሲዮን የግል ባለሀብቶች እና ሌሎች ግለሰቦች ገዝተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአክሲዮን ሽያጩ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ እና በኦሮሚያ የህብረት ስራ ባንክ ሁሉም
ቅርንጫፎች እየተከናወነ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

የኬኛ ቤቬሬጅስ አክሲዮን ማህበር የፋብሪካዎች ማዕከል የአዋሽ ምንጭ የሆነችውና በምዕራብ ሸዋ ዞን የምትገኘው ጊንጪ ከተማ መሆኗም
ነው የተገለፀው።
admin@hebrezema.info
1