ትናንት ከጅግጅጋ ተነስቶ ወደ ድሬዳዋ እየበረረ በነበረው አውሮፕላን በደረሰው አደጋ በሰው ላይ ጉዳት አልደረሰም - የኢትዮጵያ አውሮፕላን አደጋዎች ምርመራ ቢሮ

July 28,2021

ትናንት ከጅግጅጋ ተነስቶ ወደ ድሬዳዋ እየበረረ በነበረው አውሮፕላን በደረሰው አደጋ በሰው ላይ ጉዳት አልደረሰም - የኢትዮጵያ አውሮፕላን አደጋዎች ምርመራ ቢሮ


ትናንት ከጅግጅጋ ተነስቶ ወደ ድሬዳዋ እየበረረ በነበረው አውሮፕላን በደረሰው አደጋ በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱን የኢትዮጵያ አውሮፕላን አደጋዎች ምርመራ ቢሮ ገለጸ፡፡


ቢሮው ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ንብረትነቱ የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎቶች የሆነና የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኪራይ እየተገለገለበት የሚገኘው አውሮፕላን 7:13 ተነስቶ ከጅግጅጋ ወደ ድሬዳዋ እየበረረ ሳለ 33 ደቂቃ ከበረረ በኋላ መውደቁን አረጋግጧል። አውሮፕላኑ በነበረው መጥፎ የአየር ጸባይ ምክንያት ከአነስተኛ ተራራ ጋር ተጋጭቶ መውደቁን ነው ያስረዱት፡፡


ቢሮው እንዳለው በአውሮፕላኑ ሁለት የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ሠራተኞች እና ሁለት የበረራ ቡድን አባላት በአጠቃላይ አራት ሰዎች ተሳፍረው የነበረ ሲሆን፥ በተሳፋሪዎች ላይ ጉዳት አለመድረሱን ምርመራ ተደርጎላቸው መረጋገጡን ገልጿል።


በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ኮምቦልቻ ወረዳ የወደቀው ሲሲና ካራቫን 200 ቢ የተሰኘው አውሮፕላን በቅድመ ትንበያ በአየር ብልሽት ምክንያት እንደወደቀ ነው የተነገረው።


በአደጋውም በአውሮፕላኑ ላይ መጠነኛ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፥ ቀጣይ ምርመራ ለማድረግ የምርመራ ቡድን ወደ ስፍራው ማቅናቱንም ነው የቢሮው ሃላፊ ኮለኔል አምድዬ አያሌው የገለጹት። በዘመን በየነ