1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
ከዛሬዋ ሶማሊያ በስተጀርባ የዛሬዋ ኢትዮጵያ አለች
May 11, 2017
እአአ በ1991 የጀነራል ዚያድባሬ መንግሥትን መውደቅ ተከትሎ ሶማሊያ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ መንግሥት
አልባ ሆና ተጉዛለች። አገሪቱን ወደነበረችበት ለመመለስም የተለያዩ አገራት የተለያዩ ጥረቶችን አድርገዋል፡፡ አንዳቸውም
ግን ሶማሊያን አገር ማድረግ አልተቻላቸውም፡፡ የአገሪቷ ጎረቤቶች በተለይም ኢትዮጵያ ግን ሶማሊያን እንደ አገር
ለማቆም ጥረት ማድረጋቸውን አልተውም፡፡ በዚህም በመጀመሪያ በጅቡቲ፣በመቀጠል በኬንያ የሽግግር መንግሥት መመስረት
ችለው ነበር፡፡

የተመሰረተው የሽግግር መንግሥት ገና ፍሬ ማፍራት ሳይጀምር ራሱን የእስላሚክ ፍርድ ቤቶች ህብረት እያለ ይጠራ
የነበረ አሸባሪ ቡድን ዋና ከተማዋን ሞቃዲሾን ጨምሮ አብዛኛውን የአገሪቱን ክፍል ተቆጣጠረ። ታላቋን ሶማሊያ
እንደሚመሰርት በማስታወቅም በኢትዮጵያ ላይ የጀሃድ ጦርነት አወጀ። ኢትዮጵያም በሉዓላዊነቷ ላይ የተቃጣውን ስጋት
ለመቀልበስና ሶማሊያን እንደ አገር ለማቆም ጦሯን በማዝመት አሸባሪ ቡድኑን ደምስሳለች። አሁንም ድረስ የአገሪቷ
ብሎም የቀጣናው ራስ ምታት የሆነው አልሸባብ ዳግም የሶማሊያ ደንቃራ ሆኖ ብቅ አለ፡፡ አሁንም ኢትዮጵያ ጦሯን
ወደዚያው በመላክ አገሪቷን ከአልሸባብ እያጸዳች ትገኛለች፡፡

የሶማሊያ ጎረቤቶች በተለይም ኢትዮጵያ በከፈሉት ከባድ መስዋዕትነትም ዛሬ ሶማሊያዊያን በአገራቸው ላይ የሰላም አየር
መተንፈስ ጀምረዋል፤ በቅርቡም ዴሞክራሲያዊ ነው የተባለለትን ምርጫ አካሂደው ፕሬዚዳንታቸውን መርጠዋል፡፡
የቀጣናውን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎችም "ለዛሬዋ ሶማሊያ መፈጠር የዛሬዋ ኢትዮጵያ አስተዋጽኦ
ከፍተኛ ነው" ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

በኢትዮጵያ የሶማሊያ አምባሳደርን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ባይሳካም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት
የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ፤ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት የከፈለችውን
መስዋዕትነት በግልጽ በመጥቀስ ምስጋናቸውን ችረዋል፡፡ አገራቸው አልሸባብን የማሸነፍ እቅድ እንዳላት ጠቁመውም
የኢትዮጵያን እገዛ በይፋ ጠይቀዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጎረቤት አገራትና የኢጋድ ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኔ ፍስሃ፤ ሶማሊያ እንደ አገር
እንድትቆም ኢትዮጵያ ብዙ መስዋዕትነት መክፈሏን ያስታውሳሉ። በአገሪቱ የሚዋጉ ከ25 በላይ ኃይሎች ችግራቸውን
እንዲፈቱ ከ25 ጊዜ በላይ አሸማግላለች፤ በምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታትና በአፍሪካ ህብረት በኩልም መፍትሄ
አፈላልጋለች፤ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት የተባለውን አሸባሪ ቡድን ደምስሳለች፤ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር
በመሆንም የሰላም አስከባሪ ሀይል አሰማርታለች፤ በራስዋም ጦሯን ልካ አልሸባብን እየደመሰሰች ትገኛለች፤ ከአንዴም
ሁለት ጊዜ የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት ከፍተኛ ሥራዎችን አከናውናለች፤ ሶማሊያዊያን ከ25 ዓመታት በኋላ
ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂደው መሪያቸውን ለመምረጣቸውም አሁንም የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዋጋ ላቅ ያለ
መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ የሚገልጹት፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪና የጂኦ ፖለቲካል ጉዳዮች
ዲፓርትመንት ኃላፊ አቶ አበበ አይነቴ፤ ኢትዮጵያ በዋናነት ለእራሷ ደህንነት ስትል ለዛሬዋ ሶማሊያ እዚህ መድረስ
የህይወት፣ የአካል፣ የጊዜና የገንዘብ መስዋዕትነት ከፍላለች ይላሉ። ከጎረቤትና ከዓለም አቀፍ መንግሥታት ጋር
በመስራትም የሶማሊያ ጉዳይ አጀንዳ እንዲሆን በማድረግ ሰላም አስከባሪ እንዲሰማራም አድርጋለች፤ ቦጠር አበጋዞች
ትመራ የነበረችውና የአሸባሪዎችም መፈንጫ ሆኖ የኖረችው አገር ዛሬ የተሻለች አገር ልትሆን ችላለች፤ ከዚህ ድል
ጀርባ ደግሞ ዋናዋ አገር ኢትዮጵያ ናት ይላሉ አቶ አበበ፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አቶ ገብረመድህን ገብረሚካኤል እና በግጭት
አፈታቶች ዙሪያ የሚሰሩትና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ካህሳይ ገብረእየሱስ በሁለቱም ባለሙያዎች ሀሳብ ይስማማሉ፡፡
በተለይም አቶ ገብረመድህን ኢትዮጵያ ሰራዊቷን ወደ ሶማሊያ ባትልክ ኖሮ አይደለም የዛሬውን አይነት አገር ልትሆን
ይቅርና ለራሷ ለኢትዮጵያም ትልቅ ስጋት ትሆን ነበር፡፡ የከፈለችው መስዋዕትነትም የዛሬዋን ሶማሊያ ፈጥሯል፤ የራሷን
ሰላምና ጸጥታ አረጋግጧል፤ በቀጣናው የዲፕሎማሲ የበላይነትን አጎናጽፏታል፤ ፈላጊዎቿ እንዲበዙ አድርጓል፤ ለጸጥታው
ምክር ቤት በተካሄደው ምርጫ በከፍተኛ ድምጽ እንድትመረጥም አግዟታል፤ ከአሸባሪዎች ጀርባ ሆነው የኢትዮጵያን
ጥቅም ለመጉዳት ይሰሩ የነበሩ የኤርትራ፣ ግብጽ፣ ሊቢያንና ሌሎች አገራትን ሴራ አክሽፏል።

አቶ ካህሳይ በበኩላቸው እንደ አልቃይዳ፣ የእስልምና ፍርድ ቤቶች ህብረት፣ አልሻባብና ሌሎች አሸባሪ መፈልፈያ
የነበረችው ሶማሊያ ዛሬ አንጻራዊ በሆነ መልኩ የተሻለች አገር ልትሆን የቻለችው በኢትዮጵያም አስተዋጾ ነው ይሉና፤
አሁን የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሶማሊያ ካላት ስልታዊ አቀማመጥ የተነሳ የመካከለኛው ምስራቅና የምዕራቡ
ዓለም አገራት ጥቅማቸውን ለማስከበር እየተሯሯጡ ነው ይላሉ።

በተለይም ቱርክ፣ አሜሪካና እንግሊዝ ከሶማሊያም በላይ የህንድ ውቃያኖስን ለመቆጣጠር እየሠሩ ናቸው። የመካከለኛው
ምስራቅ አገራትም በሃይማኖት ያላቸውን ቅርበት በመጠቀም ብሄራዊ ጥቅማቸውን በሶማሊያ ለማስከበር መሯሯጥ
ጀምረዋል፡፡ ስለሆነም ይላሉ አቶ ካህሳይ፤ አገራቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ቀልብሰው የኢትዮጵያን ብሄራዊ ደህንነትና
ጥቅም በሚያጋልጥ መልኩ ሊጠቀሙበት ስለሚችሉ ከፍተኛ ሥራ መስራትና ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።

ከዚህ አንጻርም አቶ ካህሳይ የሚመክሩት፤ “በሶማሊያ ላይ ፍላጎት ያላቸውን የመካከለኛው ምስራቅ፣ የምዕራቡ ዓለም
አገራት ፍላጎትን በማጥናት የሶማሊያውያንና የአገራችን ብሄራዊ ጥቅም በሚያስከብር መልኩ የዲፕሎማሲ፣ የፖለቲካ፣
የጸጥታና የኢኮኖሚ ሥራ ማከናውን ያስፈልጋል፡፡ የሁለቱን አገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙት በማጠናከርም በማይበጠስ
ገመድ ማስተሳሰር የግድ ይላል። ኤርትራ ላይ ጫና ማድረግ የሚያስችል እንዲሁም ግብፆች በእጅ አዙር በሶማሊያ
ወደብና ሌሎች ነገሮችን በመጠቀም የኢትዮጵያን ጥቅም እንዳይጎዱ የሚያግዝ ሥራን መስራት ይገባል” በማለት ነው።
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲው መምህር ገብረመድህን በበኩላቸው፤ በሶማሊያ ምርጫ ቢካሄድም ብዙ የሚቀሩ ነገሮች ስላሉ
ኢትዮጵያ አሁንም ግንባር ቀደምነቷን መተው የለባትም ነው የሚሉት። አሁን ያለውን መንግሥት ይበልጥ መደገፍ፣
አልሸባብን ማክሰም፣ ከኢጋድ፣ ከአፍሪካ ህብረትና ከዓለም ህብረተሰብ ጋር በመሆን መስራት፣ ገና ቢሆንም በሶማሊያ
ከሚፈጠረው የኢኮኖሚ ግንኙነት ተጠቃሚ ለመሆን መዘጋጀት፣ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብሩ አካላት ድጋፍና
እውቅና እንዲሰጡ ማድረግ የኢትዮጵያ የቤት ሥራ ነው ሲሉ ያሳስባሉ።

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ኃላፊው አቶ አበበ፤ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በከፈለችው
መስዋዕትነት በሶማሊያ ላይ ያለው ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ያነሳሉ። ከዚህ በተጨማሪ አሁን የተመሰረተው
መንግሥት አልሸባብን በማስወገድም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ሰፊ ፍላጎት አለው። ኢትዮጵያም ቆም ብላ በማሰብ
ከዓለም የፖለቲካ አካሄድ ጋር እራሷን አጣጥማ የተከፈለውን መስዋዕትነት በተጠቃሚነት ማስቀጠል እንደሚገባት
መክረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ አቶ ብርሃኔ በመቋጫቸው ኢትዮጵያ በበዙ መስዋዕትነት እዚህ እንዲደርስ የደገፈችው የሶማሊያ
መንግሥት ይበልጥ እንዲጠናከር ትሠራለች ነው የሚሉት፡፡ የሶማሊያ ሰላምና መጠናከር የኢትዮጵያ ሰላምና እድገት
በመሆኑም ጭምር ከሶማሊያዊያንና ከሌሎቸ አፍሪካውያን ጋር በመሆን የተሟላ ጸጥታ እንዲኖራት፣ የተቋማት ግንባታን
በማጠናከር፣ ለሶማሊያውያን ነፃ የትምህርት ዕድል በመስጠት በልማት በመተሳሰር በኩል የተጀመረው ጉዞ ተጠናከሮ
እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

አጎናፍር ገዛኸኝ
admin@hebrezema.info
1