1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
ጠ/ሚ ኃይለማርያም ከፕሬዚዳንት ኤል ሲሲ ጋር መከሩ
January 30, 2017
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ኤል ሲሲ ጋር መከሩ።

ከ28ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እና ፕሬዚዳንት ኤል ሲሲ የተናጠል ውይይት
ያደረጉት።

መሪዎቹ በታላቁ ህዳሴ ግድብ እና በግብፅ በሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ሀይሎች ዙሪያ ምክክር ሳያደርጉ እንደማይቀር ተገምቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከሱዳን ፕሬዚዳንት ሀሰን አል በሽር ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።

የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያ እና ሱዳን በንግድ እና ኢንቨስትመንት እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ በሚያስችሉ
ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ሁለቱ ሀገራት ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ግንኙነታቸውን ለማሳደግም ተስማምተዋል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአውሮፓ ህብረት ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኮሚሽነር ኔቨን ሚሚካን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።

የአውሮፓ ህብረት ለበርካታ ዓመታት የኢትዮጵያን ልማት ሲደግፍ የቆየ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አስታውሰው፥ በቀጣይም
ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ውይይቱን የተከታተሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ጉዳዮች ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ካሳ
ገብረዮሐንስ ገልጸዋል።

በተለይም አገሪቱ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር ለምታደርገው ጥረት ኢትዮጵያን እንዲደግፉ ጠይቀዋል።

ህብረቱ በአገሪቱ እየተስፋፉ ባሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሳተፉና በዚህም ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከአገሪቱ ጋር እንዲሰሩ ጠቅላይ
ሚኒስትር ኃይለማርያም መጠየቃቸውን አቶ ካሳ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የአውሮፓ አገራት ባለኃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ነዋያቸውን እንዲያፈሱና ለባለኃብቶቹም መንግሥት
አስፈላጊው ትብብር እንደሚያደርግ ጠይቀዋል።

በአውሮፓ ህብረት ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኮሚሽነር ኔቨን ሚሚካን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ መስኮች የህብረቱ
ዋነኛ አጋር መሆኗን ገልጸው ይህ ወዳጅነት ለወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በተመሳሳይ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የእንግሊዝ የልማት ትብብር ሚኒስትር አምባሳደር ሱሳና ሙርሄድን አነጋግረዋል።

ከሚኒስትሯ ጋር በኢትዮጵያና እንግሊዝ መካከል ስላለው የልማት ትብብርና በአጠቃላይ ግንኙነት ዙሪያ መክረዋል።

እንግሊዝ በየዓመቱ ከ340 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ለኢትዮጵያ ልማት ድጋፍ እንደምታደርግ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ
ያመለክታል።

ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ባለፈው ዓመት በስትራቴጂካዊ አጋርነት አዲስ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

ተግባራዊነቱን ለማረጋገጥም ህብረቱ በዛሬው ዕለት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ከስምምነት መድረሱን ኢዜአ ዘግቧል።
admin@hebrezema.info
1