አዳዲስ ዘዴዎችን በመቀየስ የስራ አጥነት እና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል በትኩረት ይሰራል

October 22, 2021

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12/2014(ኢዜአ) አዳዲስ ዘዴዎችን በመቀየስ የስራ አጥነት እና የኑሮ ውድነትን በወሳኝ መልኩ ለማቃለል በትኩረት እንደሚሰራ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ።


የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አዲስ አመራሮች እና ሰራተኞች በተቋሙ በቀጣይ ስራዎች ላይ ውይይት አድርገዋል። የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል በዚህን ወቅት በኢትዮጵያ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ በመፍጠር የስራ አጥነት እና የኑሮ ወድነት ለማቃለል በትኩረት ይሰራል ብለዋል። ተቋሙ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።


በተለይ የስራ አጥነትን ችግር ለማቃለል እና ዜጎች ባላቸው ክህሎት በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ በመሰማራት ውጤታማ ስራ እንዲያከናውኑ እንሰራለን ብለዋል። ባህር አቋርጠው የሚሰደዱ ወጎኖቻችንን መታደግ የምንችለው በወሳኝ መልኩ የስራ እድል በመፍጠር ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡


በኢትዮጵያ በእውቀትና ክህሎት የበለጸገ ተወዳዳሪና ምርታማ የሰው ኃይል ለመፍጠር ይሰራል ነው ያሉት ሚኒስትሯ። አዳዲስ ዘዴዎችን በመቀየስና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ስራ አጥነትና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል እንደሚሰራም እንዲሁ፡፡


በአገሪቱ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የስራ መስኮች ተወዳዳሪና ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን ምርታማ የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት መሰጠቱንም አንስተዋል፡፡ ተቋሙ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ተወዳዳሪ የሆኑ አቅሞችን ለመፍጠር እንደሚተጋም ጠቁመዋል።


በኢንዱስትሪዎች ምቹ የስራ ሁኔታን ለመፍጠር አሰሪና ሰራተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አሰራሮች እንደሚዘረጉ የተናገሩት ደግሞ ሚኒስትር ደኤታው ዶክተር በከር ሻሌ ናቸው። ተቋሙ የሰራተኞችን መብት እንዲሁም በውጭ ሀገር የሚደረግን የስራ ስምሪት የሚቆጣጠርና የሚያስተባብር ፖለሲ ከማውጣት ጀምሮ በስራ ዕድል ፈጠራና በሙያ ክህሎት ላይ አተኩሮ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡