1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
admin@hebrezema.info
የኢትዮ ቴሌኮም ምክትል ስራ አስኪያጅ በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ
January 12, 2017
የኢትዮ ቴሌኮም ምክትል ስራ አስኪያጅ እና የኩባንያው የሶርሲንግ እና ፋሲሊቲ ዲቪዥን ሀላፊ አቶ አብርሃም ጓዴ በሙስና ወንጀል
ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

አቶ አብርሃም ጓዴ ከከረዩ ቱር ኤንድ ትራቭል ስራ አስኪያጅ ጋር በመመሳጠር ኢትዮ ቴሌኮም ከፈፀመው የውል ስምምነት ውጪ የምርት
ዘመናቸው ከአውሮፓውያኑ 2000 ዓመተ ምህረት እና ከዚያ በኋላ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ለኢትዮ ቴሌኮም መቅረብ ሲገባቸው
ከአውሮፓውያኑ 2000 ዓመተ ምህረት በፊት የሆኑ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን እያወቁ የተሽከርካሪዎቹን ምርመራ ከሚያደርገው
ድርጅት ጋርም በመመሳጠር ምርመራውን እንዲያልፉ በማድረግ በመንግስት ላይ ኪሳራ እንዲደርስ በማድረግ የሙስና ወንጀል
ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ፖሊስ በዚህ መንገድ ኢትዮ ቴሌኮም 67 ተሽከርካሪዎችን እንደተከራየ ቢገልፅም በመንግስት ላይ የደረሰውን ኪሳራ መጠን
አላስቀመጠም።

ተጠርጣሪው ታህሳስ 18 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት በቁጥጥር ስር ውለው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ሁለተኛ
የወንጀል ችሎት ዛሬ ቀርበዋል።

የተጠርጣሪው ጠበቃ መርማሪ ፖሊስ ምርመራውን በማጠናቀቁ በዋስትና ሊለቀቁ ይገባል ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ምርመራየን ስላላጠናቀኩኝ ቢለቀቁ ሰነድ ሊሰወርብኝ ይችላል በሚል ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን እንዳይቀበል
ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም የሁለቱን ክርክር ካደመጠ በኋላም ብይን ለመስጠት ለፊታችን ሰኞ ጥር 8 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሌላ ዜና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሙዪኒኬሽን ሃላፊ የሆኑት እና እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ2012/13 የእቃ አቅርቦት እና
አስተዳደር ሃላፊ የነበሩት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በ2012/13 በጀት ዓመት የግዢ አጽዳቂ ኮሚቴ ያልቀረበ የ500 ሺህ የቼክ ማርከር
ግዢ ጋር በተያያዘ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

በደንቡ መሰረት በአግባቡ የግዢ ፍላጎቱ ለኮሚቴ ቀርቡ በተገቢው መልኩ ግዢ እንዲፈጸም መደረግ ሲገባው የ5 ሺህ ማርከር ግዢ
ፍላጎትን መነሻ አድርገው 500 ሺህ ማርከር እንዲገዛ አድርገዋል።

ይህም በባንኩ ላይ የ6 ሚሊየን 962 ሺህ 90 ብር ከ30 ሳንቲም ኪሳራ በማድረሱ ምክንያት በቀረበ ጥቆማ በቁጥጥር ስር ውለው ዛሬ
ከሰዓት በኋላ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ የወንጀል ችሎት ቀርበው ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸዋል።

ተጠርጣሪው ፍርድ ቤት ቀርበው በማናጅመንት በተሰጠኝ አቅጣጫ መሰረት ነው ግዢውን የፈፀምኩት ብለዋል።

ማርከሩን አሁንም ባንኩ ለአገልግሎት እየተጠቀመ በመሆኑ ጉዳት ደርሷል ተብሎ ልጠረጠር አይገባም፤ የዋስትና መብቴም መከበር
አለበት ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ተጨማሪ ምርመራ እያደረኩ በመሆኑ ዋስትና ሊፈቀድ አይገባም ሲል ተከራክሯል።

እንዲሁም ለምርመራ የ14 ቀን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ ሲልም ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም የሁለቱን ወገን ክርክር አድምጦ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ ለጥር 15 ቀን 2009 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰዓት
ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የቡና የወጪ ንግድ ቅሌት


በቡና የወጪ ንግድ ቅሌት ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ተጨማሪ ሶስት የንግድ ሚኒስቴር የስራ ሀላፊዎች በቁጥጥር ስር
ውለው ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል

ተጠርጣሪዎቹ፥ 1ኛ ሁምኔሳ አብደታ፣ 2ኛ ታምራት ሀይሌ፣ 3ኛ ሜሮን ገብሬ ናቸው።

1ኛ እና 2ኛ ተጠርጣሪዎች የቡና ላኪነት ንግድ ፈቃድ በመስጠት፣ 3ኛ ተጠርጣሪ በንግድ ሚኒስቴር በቡና ገበያ መረጃ እና ቁጥጥር የስራ
ዘርፍ በሃላፊነት ተመድበው በመስራት ላይ እያሉ በመንግስት የተሰጣቸውን ስልጣን እና ሃላፊነት ወደ ጎን በመተው ከነጋዴ ባለሀብቶች ጋር
በጥቅም በመመሳጠር ከ2000 እስክ 2007 ዓ.ም ድረስ ከ56 በላይ ትክክለኛ የቡና ነጋዴ ላልሆኑ ግለሰቦች የቡና ላኪነት የብቃት
ማረጋገጫ በመስጠትና የንግድ ፈቃድ እንዲያወጡ በማድረግ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቡና ገዝተው በኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉሙሩክ
ባለስልጣን በኩል ወደ ውጭ እንዲልኩ ቁጥጥር ማድረግ ሲገባቸው ቁጥጥር ባለማድረጋቸው ቡና ወደ ውጭ ሀገር እንዲላክ ባለመደረጉ
ሀገሪቷ ማግኘት የነበረባትን ከ75 ሚሊየን 766 ሺህ 960 የአሜሪካ ዶላር በላይ አሳጥተዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ተጠርጣሪዎቹም በዛሬው እለት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ የወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

ፖሊስም በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ ለማድረግ የ14 ቀን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል።

በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ የወንጀል ችሎት ጉዳዩን መርምሮ ብይን ለመስጠትም ለነገ ጥር 5 2009 ከሰዓት
በኋላ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።በታሪክ አዱኛ
1