የታላቁ ህዳሴ ግድብ 2ኛው ዙር ውሃ ሙሌት ግድቡ የታችኛውን ተፋሰስ አገራት እንደማይጎዳ በተግባር ያረጋገጠ ነው –የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

July 23,2021

የታላቁ የህዳሴ ግድብ የ2ኛው ዙር ውሃ ሙሌት ግድቡ የታችኛውን ተፋሰስ አገራት እንደማይጎዳ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለፀ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ባሳለፍነው ሳምንት በተለያዩ መስኮች የተደረጉ ዋና ዋና የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።


በዚህም በፖለቲካው ዘርፍ 6ኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን መሰረት በማድረግ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የደስታ መግለጫ ማስተላለፋቸውን ገልጸዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ጋር ተገናኝተው ውይይት ማድረጋቸውንም ነው የተናገሩት።


በውይይታቸውም 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ፣ታላቁ የህዳሴ ግድብና የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ገለፃ መደረጉን አንስተዋል። በተጨማሪ የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገው ጫና ተገቢ አለመሆኑን ለልዩ ተወካዩ ገለጻ መደረጉንም ነው ቃል አቀባዩ ያነሱት። በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ኬኒያ የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ከአገራቱ መሪዎች ጋር ተገናኝተው በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ምክክር ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።


ግድቡን በሚመለከት በሶስትዮሽ ድርድር በተቀመጠው አግባብ መሰረት ለሱዳንና ግብጽ በደብዳቤ እንዲያውቁት ተደርጎ 2ኛው ዙር የውሃ ሙሌቱ መከናወኑንም አምባሳደር ዲና ገልፀዋል።


የውሃ ሙሌቱ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የትኛውንም የተፋሰስ አገራት እንደማይጎዳ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም ነው የገለጹት። ከሰሞኑ ሱዳን የጎርፍ መጥለቅለቅ አጋጥሟት እንደነበር አስታውሰው፤ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በሱዳን ተጨማሪ የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት ማድረጉን ተናግረዋል። ይህም ግድቡ ለሱዳን ያለውን ጠቀሜታ አመላካች ነው ብለዋል።


በደቡብ አፍሪካ ተቀስቅሶ በነበረው ሁከት ህይወቱ ያለፈ ኢትዮጵያዊ አለመኖሩን ጠቅሰው፤ ነገር ግን በሁከቱ አካል መቁሰልና ንብረት ዘረፋ የደረሰባቸው ኢትዮጵያዊያን አሉ ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ኢምባሲ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ዜጎችን ለመታደግ ጥረት እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል ። እስካሁን ባለው ሂደት 41 ሺህ ዜጎችን ከሳውዲ አረቢያ ወደ አገር ቤት መመለስ መቻሉንም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።